የሲዳማ ክልል ይፋዊ ምሥረታ ሥርዓት እየተካሔደ ነው
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ
“ኢትዮጵያ በፌስቡክና በዩቲዩብ ጫጫታ አትፈርስም” ሽመልስ አብዲሳ
ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 22, 2021)፦ አስረኛው የኢትዮጵያ ክልል በመኾን ባለፈው ዓመት በተካሔደ ሕዝበ ውሳኔ የተረጋገጠው የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት ይፋዊ ምሥረታ ሥርዓት ዛሬ በሐዋሳ እየተካሔደ ነው።
በዚህ የምሥረታ በዓል ላይ ለመታደም የፌዴራልና የክልል ባለሥጣናት በሐዋሳ ተገኝተው ሥርዓቱን እየታደሙ ይገኛሉ። የሲዳማ ክልል ባለሥልጣናትም የሲዳማ ክልል ኾኖ እንዲወጣ የለውጡ አመራር ያሳየውን ቁርጠኝነት በማስታወስ ምስጋና አቅርበዋል።
የተለያዩ ክልል ፕሬዝዳንቶችና ተወካዮችም አጋርነታቸውን ለመግለጽ ንግግር አድርገዋል።
በተለይ በዚህ የምሥረታ ሥርዓት ላይ ከተገኙት የክልል ፕሬዝዳንቶች መካከል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የሲዳማ ወጣት ላለፉት አሥርት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጎ ባመጣው ፍሬ የሲዳማ ክልል ተመሥርቷል፤ የትግሉ ሰማዕታት ዛሬ ይህንን ፍሬ በማየታቸው በደስታ ዕረፍት ይሰማቸዋል ብለዋል።
የሲዳማ ሕዝብ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ጎሣ፣ ቋንቋ እና ባህል የሚጋራ፤ በክፉ ጊዜ ሁሉ አብሮ የኖረ እና ወደፊትም አብሮ የሚቀጥል እንደኾነም የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ጋር ኢትዮጵያን ከነበረችበት ውድቀት የማውጣት እና ወደ ብልጽግና ማማ ከፍ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ከፊታችን ስላለ ሁላችንም ቆርጠን እንነሳ ብለዋል።
የኢትዮጵያዊነት መንገድ እኩልነት፣ ወንድማማችነት፣ ነፃነት፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ እንደኾነ ያመለከቱት ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚህ ውጭ ያለው መንገድ ሁሉ የጥፋት ስለመኾኑም በዚሁ የሲዳማ ክልል ምሥረታ ፕሮግራም ላይ ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ጥፋት መንገድ አትሔድም፤ እንዲሁ እንዳማረች፣ ሕብረ-ብሔራዊነቷን እያረጋገጠች፣ አንድነቷን እያጠናከረች ብልጽግናዋን ታረጋግጣለች” በማለት ያከሉት አቶ ሽመልስ፤ “ኢትዮጵያ በፌስቡክ ጫጫታ እና በዩቲዩብ ጩኸት የምትፈርስ የምትመስላቸው ወገኖች፤ ኢትዮጵያ የማትፈርስና አፍራሾቿን ሁሉ እያፈረሰች፤ አንድነቷን ጠብቃ ትቀጥላለች” በማለት ተናግረዋል።
ይህ እንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ ክልል ለሲዳማ ክልል የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚያደርግ በዚሁ ሥርዓት ላይ ተገልጿል። ይህንንም አቶ ሽመልስ በፕሮግራሙ ላይ አሳውቀዋል።
በተመሳሳይ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም የአዲስ አበባ አስተዳደር ለሲዳማ ክልል ማቋቋሚያ የሚኾን የ50 ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውና የዚህንም ገንዘብ ቼክ ለሲዳማ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ አስረክበዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከኦሮሚያ ክልል ሌላ ዛሬ ለሲዳማ ክልል ድጋፍ መስጠታቸውን ከገለጹት ውስጥ የአማራ ክልል 10 ሚሊዮን ብር፣ የሐረሬ ክልል አምስት ሚሊዮን ብር፣ የአፋር ክልል ሰባት ሚሊዮን ብር፣ የጋምቤላ ክልል ሁለት ሚሊዮን ብር መስጠታቸው ታውቋል።
ከዚህም ሌላ የአርሲ ዞን አንድ ሚሊዮን ብር፣ የሻሸመኔ አስተዳደር ደግሞ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ተጠቅሷል። በዛሬው ዕለት ለሲዳማ ክልል የተሰጠው ጠቅላላ ድጋፍ 205 ሚሊዮን ብር ነው። (ኢዛ)



