ለትግራይ ለእርዳታ የመጣን እህል ለመውሰድ የሞከሩ አሥር ግለሰቦች ተያዙ
ሽሬ ከተማ
የእርዳታ እህሉ ለሽሬና አካባቢዋ ነዋሪዎች ሊሰጥ የታሰበ ነው
ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 25, 2021)፦ ለትግራይ ክልል ከፌዴራል መንግሥት ለእርዳታ የተላከን እህል በሕገወጥ መንገድ በማውጣት ሊጓጓዝ ሲል መያዙን እና በድርጊቱ የተጠረጠሩት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ።
በሕገወጥ መንገድ ሊጓጓዝ ነበር የተባለው የእርዳታ እህል ከ800 ኩንታል በላይ ሲሆን፤ ይህ እህል ለሽሬ ከተማ እና በአካባቢዋ ለሚገኙ ነዋሪዎች ሊከፋፈል የታቀደ እንደነበር ታውቋል። የሽሬ ከተማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የጸጥታ ኃላፊ ሻለቃ አብርሃም አረሩ እንደገለጹት፤ በሕገወጥ መንገድ ተጭኖ ሊጓጓዝ ሲል የተያዘው፤ ሕብረተሰቡ ለመከላከያ ባደረገው ጥቆማ ነው።
እንደመረጃው በሕገወጥ ድርጊቱ ግንኙነት ያላቸው የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦችና ሦስት አሽከርካሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ለትግራይ ክልል ከሚሰጡ የሰብአዊ እርዳታዎች ጋር ተያይዞ በተመሳሳት መልኩ ይፈጸማሉ የተባሉ ሕገወጥ ድርጊቶች እየተሰሙ ሲሆን፤ በአንዳንድ አካባቢዎችም የሕወሓት ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች ለእርዳታ የሚቀርበውን እህል ለመዝረፍ ሙከራ ስለማድረጋቸው ይነገራል። (ኢዛ)



