Prosperity Party

ብልጽግና ፓርቲ

“በማይካድራ፣ ሑመራ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ዳንሻ፣ ራያ፣ አላማጣ፣ ኮረም ወዘተ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አፈናቅላለች”

ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 3, 2021)፦ ሕወሓት በአማራ ሕዝብ ላይ ላደርሰው ግፍና መከራ ለተጎዳው ሕዝባችን ተመጣጣኝ ካሣ ያስፈልገዋል በማለት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ።

የፓርቲው የመረጃ ገጽ (ፌስቡክ) ላይ “ካሣ ያስፈልገናል” በሚል ርዕስ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘው ተሻገርን ምስል ይዞ በወጣው በዚህ ጽሑፍ፤ “ትሕነግ ላለፉት 30 ዓመታት በአማራ ላይ ላደረሰችው ግፍና መከራ ተመጣጣኝ ካሣ ለተጎዳው ሕዝባችን ያስፈልጋል” ብሏል።

አያይዞም “በማይካድራ፣ ሑመራ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ዳንሻ፣ ራያ፣ አላማጣ፣ ኮረም ወዘተ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አፈናቅላለች። ተቆጥረው በማያልቁ የጅምላ መቃብሮቿ ሺህዎች በጅምላ ተቀብረዋል፤ በቅርቡ በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሕ የአማራ ተወላጆች በማይካድራ በግፍ በጅምላ ተቀብረዋል፤ በሺህ የሚቆጠሩ ሕፃናት ወላጅ አልባ ኾነዋል፤ አዛውንቶች ጧሪ ቀባሪ የላቸውም። ሚሊዮኖች ተሰደድዋል፣ በርካታ ወጣቶች የት እንደደረሱ አይታወቅም።” በማለት ገልጿል።

“ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ በሚሊዮን የሚቆጠረው አማራ በቋንቋው አይናገርም፣ አይማርም፣ ባህልና ወጉን ተነጥቋል። ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሳይቆጠር ተዘሏል ወይም ተቀንሷል። በኢኮኖሚ አሻጥር ደሃ ኾኖ እንዲኖር ተደርጓል።” የሚለው ይኸው የፓርቲው ጽሑፍ መቋጫውን ያደረገው፤ “ታዲያ ለዚህ ሁሉ ግፍ ተፍሎ የሚያልቅ እዳ ያለበት ወገን እንዴት ተመልሶ ሊከሰን ሲዳዳ እንኳን አያፍርም?” በማለት ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ