ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ኮምፕሌክስ ሊገነባ ነው
ከግራ ወደ ቀኝ፤ የቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማያም ደሳለኝ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ አቶ ብዙአየሁ ታደለ እና የቻይና ሸሪካቸው የኾነው የቻይና ኩባንያ ተወካይ፤ (ፎቶ - ኢዛ)
ግንባታውን ከቻይና ሸሪኩ ጋር ያካሒዳል
ኢዛ (ሐሙስ የካቲት ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 4, 2021)፦ በኢትዮጵያዊው ባለሀብት አቶ ብዙአየሁ ታደለ ባለቤትነት የሚታወቀው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ፤ ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከቻይና ሸሪኩ ጋር በመኾን የሚያገነቡት የለሚ ናሽናል ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።
ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እንሳሮ ወረዳ የሚገነባው ይህ ኮምፕሌክስ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠው ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ዛሬ ሐሙስ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው።
ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ይህንን ኮምፕሌክስ የሚገነባው ዌስት ቻይና ሲመንት ከተባለ ኩባንያ ጋር ሲሆን፤ ሲሚንቶ ፋብሪካውን ጨምሮ የመስታወት፣ የጂፕሰም ቦርድ እና ሌሎች ምርቶችንም ማምረቻዎች የሚያካትተው ይኽ ኮምፕሌክስ፤ በ270 ሔክታር ቦታ ላይ የሚገነባ ነው። ግንባታው በሰባት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ይኾናል።
በኮምፕሌክሱ ከሚጠቃለሉ ማምረቻዎች ውስጥ ግን፤ የሲሚንቶ ማምረቻው በ18 ወሮች ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ማምረቻዎች በየደረጃው በሰባት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቁ መኾኑን የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ሊቀመንበር አቶ ብዙአየሁ ታደለ ገልጸዋል።

አቶ ብዙአየሁ በመሠረት ድንጋይ የማስቀመጡ ፕሮግራም ላይ ጨምረው እንደገለጹት፤ ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር (ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ) ወጪ ከሚጠይቀው የኢንቨስትመንት ወጪ ውስጥ፤ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ 11 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠበቅበት ሲሆን፤ ይህም የመጀመሪያ ደረጃ ወጪው እንደሚኾን አስታውቀዋል። ቀሪው የኢንቨስትመንት ወጪ የተጣማሪያቸው የቻይናው ዌስት ቻይና ሲመንት ሊሚትድ እና ለዚሁ ኢንቨስትመንት ብድር ለመስጠት በተዘጋጁ ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት የሚሸፈን ነው።
ከኮምፕሌክሱ ቀድሞ ግንባታው የሚጠናቀቀው የሲሚንቶ ፋብሪካ፤ በቀን 10 ሺህ ቶን የማምረት አቅም ያለው መኾኑ ታውቋል። በአጠቃላይ ከ6 ሺህ እስከ 10 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥረው ይኽ ኮምፕሌክስ፤ በተያዘለት ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በዛሬው ዕለት ለዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴም፤ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ መኾኑን አስታውቀዋል።
በዚሁ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ እንዲህ ያለው ግንባታ በአካባቢው መገንባቱ አስፈላጊ ስለመኾኑ ጠቅሰው፤ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይጠናቀቅ ዘንድ፤ የክልሉ መንግሥትም ኾነ የፌዴራል መንግሥትን በመጠየቅ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
በዚህ የመሠረት ድንጋይ የማቀመጥ ሥነሥርዓት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ተገኝተው ነበር።
ግንባታው የሚካሔድባት የእንሳሮ ወረዳ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የምትገኝ ነች። (ኢዛ)




