የአሜሪካ መንግሥት ማብራሪያ ኢትዮጵያን አስቆጥቷል
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን
የኢትዮጵያ መንግሥት የሚኒስትሩን የአንቶኒ ብሊንከንን ክስ ሐሰተኛ እና መሠረተ ቢስ ውንጀላ ነው ብሎታል
ኢዛ (ቅዳሜ መጋቢት ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 13, 2021)፦ የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ ክልል ጉዳይ እየሰጠ ያለው መግለጫ በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞ እየቀረበበትና እውነታውን ያላገናዘበ መኾኑ መገለጽ ከጀመረ ሰነባብቷል።
ከትናንት በስቲያ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትግራይ የዘር ማጽዳት ድርጊት ሲሉ መናገራቸው ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል የበለጠ ቁጣ የቀሰቀሰ ኾኗል።
አንቶኒ ብሊከን እንዲህ ያለውን መግለጫ የሰጡት፤ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ለኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው።
ይህ የአንቶኒ ብሊንከን ማብራሪያ ከተደመጠ በኋላ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚኒስትሩን መግለጫ በመቃወም ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ የአንቶኒ ብሊንከን ክስ ሐሰተኛ እና መሠረተ ቢስ ውንጀላ መኾኑን በማስታወቅ ድርጊቱን አውግዟል።
በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ መሠረት በትግራይ ክልል ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በፊትም ኾነ በኋላ፤ አንድ አካል ላይ ትኩረት ተደርጐ ምንም ዐይነት የዘር ማጽዳት ዘመቻ አለማካሔዱን አስታውቋል።
በመኾኑም በአንቶኒ ብሊንከን የተሰጠውን ማብራሪያ ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ መንግሥት የማይቀበለው መኾኑን በዚሁ መግለጫ ላይ አስፍሯል።
በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ ፖለቲካዊ ከሚያደርጉ አካላት ውጭ፤ ከአገር ውስጥና ከውጭ አጋሮች ጋር ፍትሕ እንዲሰፍንና የማጣራቱ ሒደት በፍጥነት እንዲከናወን የኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ አቋሙን ይፋ ማድረጉን ያስታወሰው ይኸው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አመልክቷል። (ኢዛ)



