National Bank of Ethiopia

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

“የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት በአብዛኛው በጥሬ ገንዘብ ላይ ተመሥርቶ የሚንቀሳቀስ በመኾኑ፤ በእጅ የሚያዝ ገንዘብ በመቶ እና በሁለት መቶ ሺህ ብር መገደቡ ተጽእኖ ማምጣቱ አይቀርም” ኢኮኖሚስቶች

ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 15, 2021)፦ መንግሥት ከባንክ ውጭ በእጅ ሊያዝ የሚችለውን የገንዘብ መጠን ከ1.5 ሚሊዮን ብር ወደ 100 ሺህ እና 200 ሺህ ብር እንዲወርድ ያመጣው መመሪያ አነጋጋሪ ኾኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን አሻሻሽሎ ባወጣው መመሪያ መሠረት ከባንክ ውጭ በእጅ መያዝ የሚኖርበት የገንዘብ መጠን በግለሰብ ደረጃ 100 ሺህ ብር፤ በኩባንያ ደረጃ ደግሞ 200 ሺህ ብር ብቻ እንዲኾን አሳውቋል።

በእጅ የሚያዝ የገንዘብ መጠንን የሚወስነው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ከሦስት ወር በፊት ሲወጣ፤ አንድ ድርጅት ወይም ግለሰብ በእጅ መያዝ የሚፈቀድለት የገንዘብ መጠን 1.5 ሚሊዮን ብር (አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር) ነበር። ከአሁን በኋላ ግን ይህ የገንዘብ መጠን በግለሰብ ደረጃ 100 ሺህ ብር እና በኩባንያ ደረጃ ደግሞ 200 ሺህ ብር እንዲኾን መወሰኑ፤ በተለያዩ የንግድ ሕብረተሰቡ አባላት እና በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጭምር ሥጋት የፈጠረ ኾኗዋል።

ይህም ሥጋት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወይም የግብይት ሥርዓት በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተ በመኾኑ፤ በእጅ መያዝ ያለበት የጥሬ ገንዘብ መጠን በዚህ ደረጃ ዝቅ መደረጉ ኢኮኖሚው ላይ ቀላል የማይባል ተጽእኖ የሚፈጥር በመኾኑ ነው።

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ያነጋገራቸው አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እንዳመለከቱት የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት በአብዛኛው በጥሬ ገንዘብ ላይ ተመሥርቶ የሚንቀሳቀስ በመኾኑ፤ በእጅ የሚያዝ ገንዘብ በመቶ እና በሁለት መቶ ሺህ ብር መገደቡ ተጽእኖ ማምጣቱ አይቀርም ብለዋል። ምክንያቱም በእጅ የሚያዘው ገንዘብ በዚህ ደረጃ መመጠኑ (መወሰኑ)፤ አንድ ነጋዴ አንድ እቃ ገዝቶ ለመሸጥ ቢፈለግ በ200 ሺህ ብር የሚገዛው እቃ ውስን ስለሚኾን ገበያው ላይ ችግር ይፈጥራል። ይህ ደግሞ አንዳንድ ምርቶች ላይ እጥረት ሊፈጥር የሚችል በመኾኑን ነው።

ይህ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ሌላው ተጽእኖ ሊሆን የሚችለው ደግሞ፤ ሰዎች በእጅ የሚይዙት የገንዘብ መጠን በተገደበ ቁጥር ለአንዳንዶች ገንዘብ ለመሸሸግ እድል የሚሰጥ በመኾኑ፤ እንደገና ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀሰውን የገንዘብ መጠን ሊጨምረው ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው።

በዋናነት ግን በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተውን የግብይት ሥርዓቱን በባንክ በኩል በሚፈጸሙ ክፍያዎች የማይካሔድ በመኾኑ፤ ያለጥርጥር የተሻሻለው መመሪያ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር ተገንዝቦ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሳያመለክቱ አላለፉም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመሪያ ሊያወጣ የቻለው በዋናነት የገንዘብ እንቅስቃሴን በባንክ በኩል ብቻ እንዲካሔድ ለማስቻል እና ጥቁር ገበያ አካባቢ ያለውን ሕገወጥ ተግባራት ለመከላከል እንደኾነ ቢታመንም፤ አሁን ያለው የግብይት ሥርዓት ከጥሬ ገንዘብ ባልወጣበት እና ተጠቃሚዎች ወደ ባንክ በመሔድ በአማራጭ የክፍያ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ በቂ ሥራ ባልተሠራበት ሁኔታ ይህንን መመሪያ መተግበር የሚያስቸግር መኾኑንም ሳይጠቀሱ አላለፉም።

ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ አሁንም ይህንን መመሪያ ከልሶ ማየት እንደሚገባው እና ይህ መመሪያ በአግባቡ እንዲተገበር ከተፈለገ ደግሞ፤ ማንኛውም ግብይት በባንክ በኩል ተፈጻሚ እንዲኾን የሚያስችል አሠራር መዘርጋት እንዳለበትም እየተነገረ ነው። አንድን ነገር ለማስተካከል ሲባል ብዙ ነገሮች የሚበላሹ ከኾነ፤ ተሻሻለ የተባለው መመሪያ የሚፈጥረው ተጽእኖ በኢኮኖሚው ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ሊያመጣ ይችላል፤ በማለት ጉዳዩ በድጋሚ መጤን አለበት ተብሏል።

በሌላ በኩል ግን በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ ግብይትን ለማስቀረት እየተሠራ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፤ እንዲህ ያለው መመሪያ አስፈላጊ ነው የሚሉ ወገኖች ደግሞ፤ የግብይት ክፍያዎች በባንክ በኩል ይሁን እያልን በእጅ የሚያዝ ገንዘብ መጠን መቀነስ የለበትም ማለት አግባብ አይደለም በማለት ይሞግታሉ። ይኼ በጥሬ ገንዘብ መገብየት አግባብ ባለመኾኑ ወደ ዘመናዊ ክፍያ ዘዴዎች እየተገባ ነውና ይህንን ለመተግበር ደግሞ የግድ ሰሞኑን በብሔራዊ ባንክ የወጣው መመሪያ ተገቢ በመኾኑ ይህን ማለማመድ ተገቢ ነው ይላሉ አዲሱን መመሪያ እየደገፉ ያሉ ወገኖች። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ