ከስምንት ሺህ በላይ ጥይቶች በአንድ ግለሰብ ቤት ተያዘ
በሲዳማ ክልል በሐዋሳ ከተማ የተያዙት ሕገወጥ መሣሪያዎች በከፊል
ሁለት መትረየሶችና 118 ሽጉጦችም ተገኝተዋል
ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 15, 2021)፦ በአንድ ግለሰብ ቤት ተከማችቶ የተገኘ ከስምንት ሺህ በላይ የተለያዩ መሣሪያዎች ጥይቶች መያዙን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
በሲዳማ ክልል በሐዋሳ ከተማ በፋራ ቀበሌ ውስጥ በአንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ ተከማችቶ ከተገኘው ከስምንት ሺህ በላይ ጥይቶች ውስጥ፤ 4,583 የሚኾኑት የቱርክ ሽጉጥ ጥይቶች ናቸው። ቀሪዎቹ 3,546 ጥይቶች ደግሞ የክላሺንኮቭ ጥይቶች መኾናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በአንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ ከተያዙት ከእነዚህ ከስምንት ሺህ በላይ ጥይቶች ሌላ 98 የቱርክ ሽጉጦች መያዛቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት አስታውቋል።
እንደዳይሬክቶሬቱ መረጃ፤ በሐዋሳ ከተማ በአንድ ግለሰብ ከተያዙት ከእነዚህ የጦር መሣሪያዎች ሌላ፤ በዚሁ በሲዳማ ክልል በጭኮ ከተማ ውስጥ በተደረገ ክትትል 30 ተጨማሪ ቱርክ ሠራሽ ሽጉጦች እና ሁለት መትረየሶችም ተይዘዋል። (ኢዛ)



