‘እንደ ቅንጅት አመራሮች የዕድሜ ልክ እስራት ይቀጡልኝ’ ዓቃቤ ሕግ

Ethiopia Zare (ዓርብ ጥር 23 ቀን 2000 ዓ.ም. February, 1,2008) ከቅንጅት አመራሮች ጋር ሕገ/መንግሥቱንና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ሙከራ ተጠርጥረው ክስ የቀረበባቸው ሁለቱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አመራሮች ጉዳያቸው ውሳኔ አግኝቶና አንቀጽ ተቀይሮ በሁለት ዓመት ከስድስት ወር እስራት ተፈርዶባቸው እስር ቤት የሚገኙ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን እንደሌሎቹ ተከሳሾች ጥፋተኛ በተባሉበትና በተቀጡበት መንገድ ጉዳያቸው መታየት ሲገባው ያለአግባብ በሌላ ወንጀል መቅጣቱ ተገቢ አይደለም በማለት የይግባኝ ቅሬታ ማቅረቡ ለማወቅ ተችሏል።

 

በሀገር ቤት የሚገኙ ዘገባዎች አንደሚያስረዱት ዓቃቤ ሕግ በዛሬው ዕለት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ እንዲሄድለት ጽፎ ያቀረበው የይግባኝ ማመልከቻ፤ አቶ ዳንኤል በቀለና አቶ ነጻነት ደምሴ ላይ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ ከአድማ ውጪ ናቸው በማለት የሰጠው ብይን አግባብ አይደለም ብሏል።

 

የዓቃቤ ሕግ ይግባኝ "ተከሳሶቹ ሲቪል ማኀበረሰቡን ለታዛቢነት በማንቀሳቀስ፣ ማኅበራቱ ከተመሠረቱበት ዓላማ ውጪ የታዛቢነትን ሥነ ምግባር የጣሱ ሕገ-ወጥ ስብሰባዎችን ጠርተዋል። በዚህም የሽግግር መንግሥት ይቋቋም፣ ምርጫ ቦርድ ፈርሶ እንደገና ይቋቋም፣ ፍርድ ቤቶች እና የመንግሥት የመከላከያ እና የደህንነት ኃይሎች እንደገና ይዋቀሩ የሚሉና ሕገመንግሥቱ ሳይፈርስ ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ ሕገ-ወጥ መግለጫዎችን በማውጣት ማኀበራቱን ለአድማው በሕገ-ወጥ መንገድ መጠቀሚያ ማድረጋቸው በማስረጃ ተረጋግጦባቸው እያለ ይህንን የሚኮነን ሕገ-ወጥ ተግባር ፍርድ ቤቱ ያለአግባብ በማወደስ በዝቅተኛ አንቀጽ ጥፋተኛ ተብለው እንዲቀጡ በማድረጉ ከባድ የሕግ ስህተት ፈጽሟል" የሚል ይዘት እንዳለው ውስጥ አዋቂ ምንጮች ጠቁመዋል።

 

በተጨማሪም "... ተከሳሾቹ 'መንግሥት ምስክሮቻችንን በማስፈራራት ጫና ያሳድርብናል' በማለት የምስክሮቻቸው ማንነት እንዳይገለጽ ሲጠይቁ ፍርድ ቤቱ ያለ አግባብ በመፍቀድ ዓቃቤ ሕግ በዱብ ዕዳ ምስክሮችን ለመስማት እንዲገደድ አድርጓል ..." በማለት ዓቃቤ ሕግ በይግባኙ ውሳኔውን ተቃውሟል።

 

በሌላ በኩል "... ተከሳሾቹ በምስክርነት የጠሯቸውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አባሎች፣ እምነት የማይጣልባቸው፣የሲቪል ማኀበረሰቡ እንቅስቃሴ መኮነን የሚገባው ነው። ምስክሮቻቸው በጥቅም የተሳሰሩ እራሳቸው ሕገ-ወጥ ተግባሮቻቸው ውስጥ የነበሩ በመሆናቸው ቃላቸው ተአማኒነት ሊኖረው አይገባም ..." ሲል ዘርዝሯል።

 

የዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶችን በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ ዋነኞቹ ቅንጅትን የሚመሩ አድመኞች ጥፋተኛ ተብለው በተቀጡበት አንቀጽ መቀጣት አለባቸው የሚል አጠቃላይ ይዘት እንዳለው ምንጮች አመላክተዋል። አቶ ዳንኤል በቀለ እና አቶ ነፃነት ደምሴ ሁለት ዓመት ከስድስት ወር ተፈርዶባቸው በቃሊቲ ማረፊያ ቤት እንደሚገኙ እና፤ እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ሁለት ዓመት ከሁለት ወር በመታሰራቸው በአመክሮ እንዲለቀቁ ለማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ጥያቄ አቅርበው የአመክሮ መብታቸውን እንደተከለከሉ ሰኞ ዕለት መዘገባችን ይታወሳል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!