አፋሮች ለጄኔራሎቹ ከፍተኛ የጦር ሜዳ ኒሻን ሸለሙ
የአፋር ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ለመከላከያ ዋና ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ኒሻኑን ሲያበረክቱ
ቤት መሥሪያ ቦታም ተበርክቶላቸዋል
ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 22, 2021)፦ በትግራይ ክልል በተካሔደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በስኬት ለመሩት የጦር መሪዎች “መላሳይ” የተባለ የጦር ማዕረግ ስያሜ የያዘ የክብር ኒሻን እና የቤት መሥሪያ ቦታ ከአፋር ክልላዊ መንግሥት ተሸለሙ።
ከክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የጦር ሜዳ የክብር ኒሻን የተበረከተላቸው የአገር መከላከያ ዋና ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ ምክትል ኤታማዦር ሹሙ ሌተናል ጄኔራል አበባው ታደሰ እና ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ናቸው።
ይህንን የክብር የጦር ሜዳ ኒሻን ሽልማቱን ያበረከቱት የአፋር ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ናቸው።
የክልሉ መንግሥት ይህንን ሽልማት የሰጠው “የአገር ክህደት ወንጀል በፈጸመው የጁንታው ቡድን ላይ የተካሔደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ በስኬት በመምራታቸው ነው” ብሏል።
በትናንትናው የሽልማት ፕሮግራም ላይ እንደተገለጸው፤ የጦር ጄኔራሎቹ ከክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ የተሰለሙት “መላሳይ” የተባለው የጦር ማዕረግ ስያሜ የያዘው ይኸው የክብር ኒሻን፤ በአፋር ሕዝብ ባህልና ወግ መሠረት ብስለት በተሞላበት የአመራር ጥበባቸው፣ በጀግንነታቸው፣ በአሮቆ አሳቢነታቸው እና በችግር ፈችነታቸው ከፍተኛ ብቃት ላላቸው ጀግኖች እና ባለታሪኮች የሚሰጥ የክብር ሽልማት ነው። (ኢዛ)



