እነ ጃዋር መሐመድ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ
አቶ ጃዋር መሐመድ (በግራ)፣ አቶ በቀለ ገርባ (መኻል) እና አርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ (በቀኝ)
በተከሰሱበት ክስ ጥፋተኛ አይደለንም አሉ
ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 22, 2021)፦ ከአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በተፈጠረው ኹከት በመጠርጠር በቁጥጥር ሥር የዋሉት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
በዛሬው (ሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም.) ችሎት በተለይ አቶ ጃዋር መሐመድ የተመሠረተባቸው ሦስት ክሶች ላይ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል፤ የተመሠረተባቸውን ክስ እንዳልፈጸሙ፣ ጥፋተኛም እንዳልኾኑ ገልጸዋል። አያይዘውም የተመሠረተባቸው ክስ እርሳቸውን እና ፓርቲያቸው ኦፌኮን ከምርጫ ለማግለል እና በሕዝብ ዘንድ መልካም ስማቸውን ለማጥፋት ነው ሲሉም ተከላክለዋል።
በተከሰሱበት ክስ ጥፋተኛ ስላለመኾናቸው የሚገልጽ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ጃዋር፤ ኦሮሞ እና አማራ የዚህች አገር ግንድ በመኾናቸው፤ ታሪካዊ ቁርሾ ተገፍፎ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ እንዲመጣ ስለመታገላቸው እና ሌሎች ተመሳሳይ ተግባራትን ስለመፈጸማቸው በዛሬው ችሎት ላይ መግለጻቸው ተሰምቷል።
ከአቶ ጃዋር ጋር የቀረቡት ሌላው የኦፌኮ አመራር አቶ በቀለ ገርባም፤ የተከሰሱበትን ወንጀል እንዳልፈጸሙ የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፤ የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራር በመኾናቸው የለውጥ መንግሥቱ ሐዲዱን በመሳቱ ሕዝብ እንዳይመርጠው በሰላማዊ መንገድ መቀስቀሳቸውን ገልጸው፤ ይህ አያስከስሰኝም ብለዋል።
አቶ በቀለም በክስ መዝገባቸው በቀረቡ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል።
በዛሬው ችሎት የተከሳሽ ጠበቆች የዋስትና ጥያቄ ይጠበቅላቸው ብለው ያመለከቱ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም ዋስትናን የተመለከቱ ጥያቄዎች በቀጣይ ቀጠሮዎች ይታያሉ ብሏል። የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ጥበቃ ጉዳይ ላይ የፊታ መጋቢት 28 ብይን የሚሰጥ ሲሆን፤ የምስክሮቹን ቃል ደግሞ ለመስማት መጋቢት 29 እና 30 እንዲሁም ሚያዝያ 5፣ 6፣ 7፥ 12፣ 13 እና 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮዎችን ሰጥቷል። (ኢዛ)



