አንጋፋው ደራሲ፣ ሃያሲውና ተርጓሚው አማረ ማሞ በሞት ተለዩ
አንጋፋው ደራሲ፣ ሃያሲውና ተርጓሚው አማረ ማሞ
ከ27 በላይ መጻሕፍትን ለአንባብያን አበርክተዋል
ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 29, 2021)፦ በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ዘርፍ በደራሲነት፣ በተርጓሚነት፣ በሃያሲነትና በአርትኦት ሥራዎቻቸው በቀዳሚነት ስማቸው ከሚነሱት መካከል አንዱ የኾኑት አንጋፋው ደራሲ፣ ተርጓሚና ሃያሲ አማረ ማሞ ከዚህ ዓለም ዛሬ በሞት መለየታቸው ተሰማ።
ከ27 በላይ መጻሕፍትን ለአንባብያን በማበርከት የሚታወቁት አማረ ማሞ፤ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር የዕድሜ ልክ የክብር አባል ነበሩ።
በአርትኦትና በሃያሲነታቸው ጭምር አበርክቷቸው የሚጠቀስላቸው አቶ አማረ ማሞ፤ የኢትዮጵያ መጻሕፍ ድርጅትን በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩም ናቸው።
አቶ አማረ ለአንባብያን ካቀረቡዋቸው መጻሕፍት መካከል እሪ በል አገሬ፣ አሳረኛው፣ ቁርበኛውና ሱዳን፣ የዴዜዴራታ ምክር፣ አግብቼሻለሁ፣ ሳቅና ቁም ነገር 110 የኤዞፕ ተረቶች የሚሉ መጻሕፍቶቻቸው የሚጠቀሱ ሲሆን፤ የአቶ አማረ መጻሕፍት፤ የልጆች ወጥ ድርሰትና የትርጉም ሥራዎችን የሚያጠቃልል ነው።
አቶ አማረ በተለይ የቀለም ጠብታ በሚል የኢ-ልብወለድ አጻጻፍ መሠረታዊ መመሪያ መጽሐፋቸው፤ እንዲሁም የልብወለድ ድርሰት አጻጻፍ የሚና ተያያዥነት ያላቸው የድርሰት መማሪያ መጻሕፍትንም ጽፈዋል።
በአርትኦት ሥራቸው ደግሞ የበዓሉ ግርማን፣ የብርሃኑ ዘሪሁን፣ የሙሉጌታ ጉደታን እና የሌሉች ደራስያንን መጻሕፍት በአርታኢነት ሠርተዋል።
ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የአቶ አማረ ማሞ፤ የቀብር ሥርዓት ከነገ በስቲያ ረቡዕ ይፈጸማል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለበርካታ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ባለሙያዎች ባለውለታ የኾኑት የታንጐ ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ዓሊ አብደላ ኤይፋ በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። በአሜሪካ በሕክምና ላይ የቆዩት አቶ ዓሊ፤ ጥላሁን ገሠሠን የሙዚቃ ሥራዎች ጨምሮ የአስቴር አወቀ፣ መሐመድ አሕመድ፣ የብዙነሽ በቀለ፣ የሒሩት በቀለ፣ የሐመልማል አባተን፣ የዓሊ ቢራን፣ የዓለማየሁ እሸቴንና የሌሎች ሙዚቀኞችን ሙዚቃዎች በሸክላና በካሴት በማሳተም የሚታወቁ ሲሆን፤ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ጉልህ የኾነ አስተዋጽኦ የነበራቸው ናቸው። የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ከትናንት በስቲያ በአሜሪካ ተፈጽሟል። (ኢዛ)



