ያላባራው ግድያ በኦሮሚያ ከሃያ በላይ ሰዎችን ነፍስ ቀጠፈ
ባቦ ጋምቤል ወረዳ (ምዕራብ ወለጋ ዞን )
በምዕራብ ወለጋው ጥቃት ጅምላ ጭፍጨፋ መኾኑን ከጥቃቱ የተረፉት ገለጹ
ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 31, 2021)፦ በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ቦኔ በሚል በምትታወቅ ቀበሌ ውስጥ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን እና መቁሰላቸው ተገለጸ። ድርጊቱ ዘር ተኮር የኾነ የጅምላ ጭፍጨፋ (ዘር ማጥፋት) ነው ሲሉ ከጥቃቱ የተረፉ የአማራ ተወላጆች ገለጹ።
ትናንት ምሽት በተከፈተው ጥቃት የሞቱት ሰዎች ከ20 ይበልጣሉ የተባለ ሲሆን፣ የሟቾቹን ቁጥር ከዚህም የሚያስበልጡና 29 ያረደርሱ መረጃዎች እየወጡ ነው።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ዘርን መሠረት ያደረገው ጥቃት አሁንም መቀጠሉን የሚያመለክተው የትናንት ምሽቱ ግድያ፤ የክልሉ መንግሥት ላይ ጫና እንዲጨምር እያደረገ ነው።
የምዕራብ ወለጋውን ግድያ ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ያወጣው መግለጫ፤ በጥቃቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገምቤል ወረዳ ቦኔ ቀበሌ ከተፈጸመው ጥቃት የተረፉ ነዋሪዎች እንደገለጹት ከኾነ፤ በንጹሐን አማራ ተወላጆች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ተናግረዋል። ትናንት ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ የታጠቁ የኦነግ ሸኔ አባላት ያሉዋቸው ወደ ነዋሪዎቹ መንደር በመግባት ንጹሐን አማራዎች ላይ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል።
እነዚህ ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች አክለው እንዳመለከቱት፤ ከዚህ ቀደም አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ሲዛትባቸው እንደነበር እና ትናንት ምሽት ዘር ተኮር የኾነ የጅምላ ጭፍጨፋ እንደተፈጸመባቸው አመልክተዋል።
ከምሽቱ 4 ሰዓት ጀምሮ የጸጥታ ኃይል በአካባቢው ቢደርስም፤ እርምጃ እንድንወስድ ስላልታዘዝን ራሳችሁን ጠብቁ ብለዋቸው እንደተመለሱም ከጥቃቱ የተረፉት ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ይህንን ዘግናኝ ድርጊት ለአማራ ማስ ሚዲያ የገለጹት እነዚህ የአማራ ተወላጆች፤ አሁንም ተደጋጋሚ ግድያ ላለመፈጸሙ ምንም ዋስትና የለንም ብለዋል። ከጥቃት የተረፉ አስተያየት ሰጪዎቹ መንግሥት በአፋጣኝ ደርሶ እንዲታደጋቸው ጠይቀዋል። (ኢዛ)



