የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በ1147 አመራር እና አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱ ተገለጸ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው
በምርጫው የጸጥታ ችግሮች እንዳይከሰቱ በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 8, 2021)፦ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 1,147 የሚኾኑ የፖሊስ አመራር እና አባላት ላይ ቀላል እና ከባድ የዲሲፕሊን እርምጃ መውሰዱ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ዛሬ (ሐሙስ መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም.) በሰጡት መግለጫ፤ ከፖሊስ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ኮምሽኑ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፣ ከፖሊስነት ሥነምግባር ውጭ በጥፋት ላይ የተገኘ አመራርም ኾነ አባላት ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ እየተወሰደ ስለመኾኑ አመልክተዋል።
በአባላቱ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች የሚስተዋሉ ግድፈቶችን በማረም ረገድ በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራ መኾኑን ገልጸው፤ በ2013 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት በ1,147 አመራር እና አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል። ኮምሽነሩ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ፖሊስ እያደረገ ያለውን ዝግጅትም አብራርተዋል።
ከምርጫው በፊት፣ በምርጫው ዕለት እና ከምርጫው በኋላ የጸጥታ ሥጋት የኾኑ ችግሮች እንዳይከሰቱ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ልዩ ልዩ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ያመለከቱት ኮምሽነሩ፤ አጠቃላይ የምርጫው ሒደቱ ፍጹም ሰላማዊ እንዲኾን በርካታ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የፌዴራል ፖሊስ በምርጫ ሒደት ዙሪያ ያወጣውን ጠቅላላ እቅድ መነሻ በማድረግ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ምርጫው ያለ አንዳች የጸጥታ እንከን በሰላም እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሰጥቶ እየተሠራ ከመኾኑም በላይ፤ መላው የኮሚሽኑ አመራር እና አባላት የምርጫ ሕጉን እና ደንቦችን ጠንቅቀው በመረዳት ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል የሚያግዝ የአቅም ግንባታ ሥልጠና የተሰጣቸው መኾኑንም ኮምሽነሩ አስታውቀዋል።
ምርጫው (ምርጫ 2013) በሰላም እንዲጠናቀቅ ያስችላሉ የተባሉ ከ4,180 በላይ አዲስ ምልምል ፖሊሶች ኮምሽኑን ተቀላቅለዋል ተብሏል።
በተጨማሪም የኮሚሽኑን የቋሚና ተወርዋሪ ኃይል በሁለት ዙር በመክፈል ለአንድ ወር ለሚቆይ ሙያ ተኮር ሥልጠና በፖሊስ አካዳሚ እየሠለጠኑ እንደሚገኙም በዛሬው መግለጫቸው ላይ አስታውሰዋል።
ኮሚሽነር ጌቱ በዛሬው መግለጫቸው ማብራሪያ የሰጡበት ሌላው ጉዳይ፤ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን የተመለከተ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የከተማችን የጸጥታ ሁኔታ በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መኾኑን በመዘገብ፤ በሕብረተሰቡ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠሩ እንደሚገኙ እና ከተገቢው የመረጃ ምንጭ ትክክለኛ መረጃ ሳይዙ ነዋሪውን ሥጋት ውስጥ የሚከቱ ግለሰቦች ኾኑ ተቋማትን በሕግ አግባብ ኮሚሽኑ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ከተማ በከባድ ወንጀሎች ላይ ተሰማርተው የነበሩ 34 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።
በከባድ ወንጀሎች ላይ ተሰማርተው የተገኙት ተጠርጣሪዎቹ በቡድን በጦር መሣሪያ በመታገዝ ትላልቅ ተቋማትን እና ድርጅቶችን ሲዘርፉ እና የድብደባ ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ መኾናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
በተደራጀ መንገድ በዘረፋ ተግባር የተሰማሩት ተጠርጣሪዎቹ፤ ውድ ዕቃዎች እና ገንዘብ ያለበትን የሚያጠና፣ ጊዜና ቦታ አመቻችቶ የሚዘርፍ እና የዘረፈውን የሚሸጥ ሦስት ቡድን እንዳላቸው የተደረሰበት መኾኑንም አስታውቋል። (ኢዛ)