ፌስቡክ በህዳሴ ግድብ ላይ ያነጣጠሩ መልእክቶችን ከግብጽ ሲያሠራጩ የነበሩ አካውንቶችን ዘጋ
ፌስቡክ
17 የፌስቡክ አካውንቶች፣ 6 ገጾች እና 3 የኢንስታግራም አካውንቶችን መዝጋቱን ገልጿል
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 8, 2021)፦ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳን እና ቱርክን ዒላማ አድርገው መረጃ ሲያሠራጩ ነበር የተባሉ እና መቀመጫቸውን ግብጽ ላይ ያደረጉ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን እንደዘጋ ፌስቡክ አስታወቀ።
ይህንን እርምጃውን የተመለከተው የፌስቡክ ኩባንያ እንዲዘጉ የተደረጉት አካውንቶቹ ከ300 ሺሕ በላይ ተከታዮች እንደነበራቸው ገልጿል።
እንደ ፌስቡክ ተጨማሪ መረጃ 17 የፌስቡክ አካውንቶች፣ 6 ገጾች እና 3 የኢንስታግራም አካውንቶችን መዝጋቱን ነው። የፌስቡክ ኩባንያ ባደረገው ምርመራ፤ የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ገጾቹ መቀመጫውን ግብጽ ያደረጉ ቢ ኢንተራክቲቭ የተባለ ማርኬቲንግ ኩባንያ አካል መኾናቸውንም ጠቅሶ፤ አካውንቶቹ ሲያሠራጩ የነበረው በኢትዮጵያ በስፋት በሚነገረው አማርኛ ቋንቋ ስለመኾኑም ገልጿል።
በፌስቡክ መረጃ መሠረት በአማርኛ ቋንቋ በእነዚህ አካውንቶች ይሠራጩ የነበሩት መልእክቶች ኢትዮጵያ እየገነባች ባለችው የህዳሴ ግድብ ላይ ያነጣጠረ ስለመኾኑም አውስቷል። (ኢዛ)



