ባለፉት ፵፭ ቀናት ከ፲፫ እስከ ፴፱ ሚሊዮን ዶላር አጥታለች

ኢትዮጵያ ዛሬ (ኀሙስ ኅዳር ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 17, 2016)፦ ዛሬ ኢትዮጵያ ኢንተርኔት ከዘጋች አርባ አምስተኛ ቀን ሆናት። ላለፉት አርባ አምስት ቀናት አገሪቱ ኢንተርኔት በመዝጋትዋ ቢያንስ ፲፫ (13) ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዳጣች የኢትዮጵያ ዛሬ የዜና ዝግጅት ክፍል ”ሴንተር ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን” ከዚህ በፊት ያወጣውን መረጃ መሰረት በማድረግ ያሰላው ስሌት ጠቆመ። ስሌቱ ያላካተታቸው መስፈርቶች ቢካተቱ ኪሳራው ወደ ፴፱ (39) ሚሊዮን ዶላር ሊጠጋ ይችላል።
ሴንተር ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን በኦክቶበር 2016 እ.ኤ.አ. ያወጣው ስሌት ያተኮረው በኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ኪሳራ እንጂ፣ ያላካተታቸው በርካታ መስፈርቶች እንዳሉ በሪፖርቱ ገልጿል። ድርጅቱ ኪሳራውን ለማስላት ያላካተታቸው መስፈርቶች፤ መንግሥት የሚያገኘው ቀረጥ፣ ኢንቨስተሮችና የንግድ ተቋማት የሚደርስባቸው ኪሳራ፣ በተጠቃሚ ማኅበረሰብ ላይ የሚደርሱት ኪሳራዎች፣ የንግድ ፈቃድ አውጥተውም ሆነ ሳያወጡ ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ ገቢ የሚያገኙ ግለሰቦች፤ ከብዙ ጥቂቶቹ እንደሆኑ ለመረዳት ችለናል።
ባልተካተቱት መስፈርቶች መሰረት ኢትዮጵያ ምን ያህል ኪሳራ እንደሚደርስባት የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም፤ በሴንተር ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ በቀን 284645 የአሜሪካ ዶላር ታጣለች። በወር ከ12 ሚሊዮን 809 ሺህ ዶላር በላይ ኪሳራ ይደርስባታል፤ ይህ አኀዝ ኢትዮጵያን ለመሰለች ከዓለም ድሃ አገሮች ተርታ ለምትገኝ አገር ቀላል እንዳልሆነ ይታመናል። ያልተካተቱት መስፈርቶች ቢጨመሩ አኀዙ ቢያንስ በሦስት እጥፍ ከፍ ሊል እንደሚችል በጉዳዩ ላይ ግምታቸውን የሰጡን ኢኮኖሚስቶች ይናገራሉ። ኪሳራው በሦስት እጥፍ እንኳ ቢሰላ ከ38 ሚሊዮን 427 ሺህ ዶላር በላይ ይሆናል።
በተለይም አዲስ አበባን ጨምሮ በትላልቅ ከተሞች የሚገኙ የኢንተርኔት ካፌዎች፣ ፊልም ማከራያ ድርጅቶች፣ አስመጪና ላኪዎች በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ እንደገጠማቸውና አንዳንዶቹም ምንም አይነት ገቢ ላለፉት አርባ አምስት ቀናት እንዳላገኙ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጠዋል።
ሞኖፖሊስቱ የኢትዮቴሌኮም ለተወሰኑና እሱ ለፈቀደላቸው አንዳንድ ድርጅቶች የኢንተርኔት አገልግሎቱን ያልነፈጋቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ለማረጋገጥ ችሏል። ምንም እንኳን የተመረጡ ድርጅቶችና ተቋማት ኢንተርኔት የተፈቀደላቸው ቢሆንም፤ ይህ ፈቃድ በአገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችንና ኮሌጆችን ያላካተተ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ዓለማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና አዋሳ ዩኒቨርስቲዎች ሊጠቀሱ የሚችሉ ሲሆን፤ መምህራንና ተማሪዎች የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ እንቅፋት መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ዘገባ ያስረዳል። ከዚህም ሌላ በዩኒቨርሲቲዎቹ የሚገኙ ተማሪዎችና አስተማሪዎች ከውጭ አገርም ሆነ ከአገር ውስጥ ያገኟቸውን ሥራዎች (ገቢ የሚያስገኙ እና የጥናትና ምርምር) መሥራት እንዳልቻሉ ለመረዳት ችለናል።
በስደት ላይ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደቀድሞው ሊገናኙ ባለመቻላቸው እየተማረሩ ሲሆን፣ የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎችም ጭምር እንደወትሮው ከቤተሰቦቻቸው ጋር በቫይበር፣ ዋትስ አፕ፣ ስካይፕ፣ ኢሞ፣ ፌስቡክ፣ ... መገናኘት አለመቻላቸው እንዳስከፋቸው የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ያነጋገራቸው ስደተኞች ገልጠውለታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎቱን ያገደው ከመስከረም ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. (ኦክቶበር 4 ቀን 2016) ጀምሮ ሲሆን፣ ከአራት ቀናት በኋላ መስከረም ፳፰ ቀን ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአገሪቱ ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው አይዘነጋም። ለአዋጁ መነሻ የሆነው ምክንያት በአገሪቱ የተቀሰቀሰው የሕዝብ እምቢተኝነት መሆኑ ይታወቃል።



