በእነ ጃዋር መሐመድ ላይ በግልጽ ችሎት ሊሰማ የነበረው የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል እንዳይሰማ ታገደ

አቶ ጃዋር መሐመድ (በግራ)፣ አቶ በቀለ ገርባ (በቀኝ) እና የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዓርማ (ከጀርባ)
አቶ በቀለ ገርባ የኮቪድ 19 ክትባት እንዲሰጣቸው ጠየቁ
ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 13, 2021)፦ ባሳለፈው ሳምንት በእነ ጃዋር መሐመድ ላይ በዝግ ችሎት የምስክሮቼን ላሰማ የሚል ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት ዓቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ፤ ከዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በግልጽ ችሎት ሊሰማ የነበረው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል እንዳይሰማ አሳገደ።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በቀደመው ቀጠሮ ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ብይን የሰጠ ቢኾንም፤ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቼ ለደኅንነታቸው ሲባል ከመጋረጃ ጀርባ እንዲደመጡ ያለው አቤቱታው ውድቅ መደረጉን በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤት በማለቱ፤ ዛሬ ሊሰማ የነበረው የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃልም ሳይሰማ ቀርቷል።
የዓቃቤ ሕግ የምስክሮች ቃል ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ይካሔዳል የሚል ብይን በከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሰጥቶ የነበረ መኾኑን መዘገባቸውን አይዘንጋም።
ይህንኑ በዛሬ ችሎት ይፋ ያደረገው ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በነገው ዕለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሒደቱ ላይ ተከሳሾች በፕላዝማ ቀጥታ ከማረሚያ ቤት የቃል ክርክር እንዲያደርጉ ትእዛዝ መተላለፉን የጀርመን ድምፅ ዘግቧል።
ይህ በአንዲህ እንዳለ፤ በእነ ጃዋር መሐመድ የክስ ምዝገብ ውስጥ የተካተቱት አቶ በቀለ ገርባ በዛሬው ችሎት የኮቪድ 19 ክትባት እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ እንዲያስተላልፍላቸው ጠይቀዋል። ጤና ሚኒስቴር ባወጣው መስፈርት መመዘኛ መሠረት ክትባቱን ማግኘት እችላልሁና ይፈቀድልኝ ባሉት መሠረት፤ ፍርድ ቤቱ ክትባቱን እንዲያገኙ ማረሚያ ቤቱን አዝዟል።
ዛሬ በግልጽ ችሎት ሊሰማ የነበረው የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃል በመታገዱ ምክንያት፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ለመጠባበቅ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሚያዝያ 20 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢዛ)