የብር ኖት ቅያሬው 126 ቢሊዮን ብር ወደ ባንክ ሥርዓት እንዲገባ ማድረጉ ተገለጸ

አዲሶቹ የብር ኖቶች
7.2 ሚሊዮን አዳዲስ የባንክ ደንበኞችም አስገኝቷል
ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 27, 2021)፦ የብር ኖት ቅያሬው ከ7.2 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የቁጠባ ሒሳብ (አካውንት) እንዲከፍቱና ከ126 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወደ ባንክ ሥርዓት እንዲገባ ያስቻለ መኾኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብር ኖት ቅያሬውን በስኬታማ ሁኔታ መጠናቀቁንና ይህም እንዲኾን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ባዘጋጀው የምስጋና እና የእውቅና ፕሮግራም ላይ እንደገለጸው፤ የብር ኖት ቅያሬው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያስገኘ እንደነበርም አስታውቋል።
በአዲሱ የብር ኖት ቅያሬ ከ185 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ የብር ኖት ለባንኮች እንደተሠራጨም ተገልጿል። የብሔራዊ ባንክ 262 ቢሊዮን ብር አዲስ የብር ኖት ማሳተሙ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብር ቅያሬውን በሦስት ወር ለማጠናቀቅ የሠራ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል የተፈጠረው ችግር ሕግ በማስከበር ሥራው በትግራይ የብር ኖት የቅያሬው ጊዜ በአንድ ወር ሊራዘም ችሎም ነበር።
አጠቃላይ የብር ኖት ቅያሬው ክንውን የማጠቃለያ ሪፖርቱም ዘግይቶ በዛሬው ዕለት (ማክሰኞ ሚያዝያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም.) እንዲካሔድ የተደረገው በትግራይ ክልል የብር ኖቱ ቅያሬ ዘግይቶ በመጠናቀቁ ነው። (ኢዛ)