አበረ አዳሙ

ኮሎኔል አበረ አዳሙ

ሕይወታቸው ያለፈው በሕክምና ተቋም ውስጥ መኾኑ ተነገረ

ኢዛ (ማክሰኞ ሚያዝያ ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 4, 2021)፦ ከሳምንት በፊት ሚያዝያ 19 ቀን ከአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አበረ አዳሙ ከዚህ ዓለም መለየታቸው ታወቀ። የክልሉ መንግሥት በድንገተኛ ሕመም ምክንያት የሕክምና እርዳታ ሲደረግላቸው መቆየቱንና ሕይወታቸው ማለፉን ገልጿል።

በሰሜን ሸዋ በተለይም በአጣየ በተከሰተው ከፍተኛ የዘር ተኮር ግድያ፣ የሕዝብ መፈናቀል እና የከተማዋ ሙሉ ለሙሉ መውደም ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ባለሥልጣናት መካከል አለመግባባት መፈጠሩ በሰፊው እየተነገረ ባለበት ወቅት ነው ኮሎኔሉ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ የተደረገው።

በተለይም ከሥልጣናቸው ከመነሳታቸው ቀደም ብሎ በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች ዘር ተኮር ጥቃት ይብቃ በሚል ከተደረጉት የተቃውሞ ሰልፎች ማግስት ለግምገማ የተቀመጠው የክልሉ ምክር ቤት እና የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች፤ የክልሉን የፖሊስ ኮሚሽነር ከኃላፊነት እንዲነሱ ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው ነበር በኮሚሽነር አበረ አዳሙ ፈንታ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ የተሾሙት።

ኮሎኔሉ የዛሬ ሦስት ዓመት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በስደት ይኖሩበት ከነበረበት ስዊድን አገር ወደ አገር ቤት የገቡት። ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ያግቧቧቸው ማቹ ጄኔራል አሳምነው ጽጌ እንደኾኑ ይነገራል።

ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባለትዳር እና የሁለት ወንዶች ሕፃናት ልጆች (የ5 ዓመትና የ2 ዓመት) አባት ነበሩ። ልጆቻቸው እና ባለቤታቸው በስዊድን አገር እንደሚኖሩ የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ለማረጋገጥ ችሏል።

የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለኮሚሽነር አበረ አዳሙ ቤተሰቦች፣ ዘመዶች፣ ወዳጆች፣ ጓደኞች፣ … ልባዊ መጽናናት ይመኛል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!