በአማራው ክልል ያለው መለስተኛ ጦርነት ሳይባባስ መፍትሔ ይፈለግ
ግርማ ካሳ
- በሰሜን ጎንደር ዞን 145 ወታደሮች ተገድለዋል
- ከአዘዞ ካምፕብቻ 143 ወታደሮች ካምፑን ጥለው እስከነ ትጥቃችው ጠፍተዋል
ህወሓት ለሰላም በሮቹን በሙሉ ስለዘጋ፣ በሰላም የሚታገሉ፣ እንደ አንድነት ያሉ ፓርቲዎችን አግዶ፣ እንደ አንዱዋለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን ኦልባና ለሌሳ … ያሉ ሰላማዊ የፖለቲካ መሪዎችን አስሮ፣ ምርጫ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ብሎ፣ ዜጎች ወደ ማይፈለጉት መስመር ፊታቸውን እንዲያዞሩ ገፋፍቷቸዋል። የሰላም በር ሲዘጋ የአመጽ በር ተከፍቷል። በአሁኑ ወቅት ምንም መሸፋፈን አያስፈለግም፤ በተለይም በአማራው ክልል በአሁኑ ጊዜ መለስተኛ ጦርነት ነው ያለው።
አንዳንዶች የህዝቡን ተቃውሞ እንደ ቀላል ይቆጥሩታል። ከሚገባውም በላይ ህወሓትን አጎዝፈው ይመለከታሉ። ምናልባት ህወሓቶችም ራሳችው፣ ለብሔራዊ እርቅ እስከ አሁን ድረስ በራቸውን የዘጉት፣ ለራሳቸው ከፍተኛ ግምት ስለሰጡና ህዝቡንም ስለናቁት ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
እርግጥ ነው የህወሓት ሠራዊት መሳሪያ የታጠቀ ኃይል ነው። ያኔ ደርግ እንደነበረው ማለት ነው። ግን የመሳሪያ ብዛት በራሱ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። መሳሪያና ትጥቅ አስፈላጊነቱ እንደተጠበቀ፣ ጦርነት የሚደረግበት አካባቢ ሁኔታ፣ የወታደሮች ሞራልና ስሜት፣ የስለላ መረጃ የመሳሰሉትን የየራሳችው ትልቅ አስተዋጾ አላቸው። እንደ ደርግ በአፍሪካ የታጠቀ ሠራዊት አልነበረም። ወደ 500 ሺህ የሚሆን ወታደር ነበር። በመሳሪያና በወታደር ብዛት ቢሆን ደርግ አይሸነፍም ነበር። ያ ጦር ግን የተሸነፈው አንደኛ ወታደሩ ስለተሰላቸና ሻዕቢያና ወያኔም በቀጥታ ቅድመ መረጃዎች ያገኙ ስለነበረ ነው። ወያኔና ሻዕቢያ ደርግን ያሽነፉት ተዋግተው ሳይሆን በሳቦታጅ ነበር። አሁን ያለው የህወሓት ሠራዊትም ከደርግ ሠራዊት በምንም አይለየም።
ህወሓቶች አንደኛ በአማራው ክልል የታጠቁ ኃይላት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴዎች የማወቅ እድል የላቸውም። ያ ብቻ አይደለም፤ እነማን እንደሆኑም አያውቅም።
ሁለተኛ በኮንቮይ ከአዲስ አበባ ይሁን ከመቀሌ ወታደሮች መንቀሳቀስ ሲጀምሩ በቀላሉ መረጃዎች ይወጣሉ። የአማራው ክልል መሬቶችም አስቸጋሪ እንደመሆናቸው በወታደራዊ ኮንቮዩ ላይ ጥቃቶችን በመፈጸም ወይንም መንገዶችን በመዝጋት የጦሩን እንቅስቃሴ መግታት ወይንም ማጓተት ቀላል ነው የሚሆነው።
ሦስተኛ መሬቱን የማያውቅ ወታደር፣ ከባባድ መሳሪያ ቢሸከምም፣ ጉድጓድ ሸንተረሩን ከሚያውቅ የአካባቢው ታጣቂ ጋር መፋለሙ ለርሱ አስቸጋሪ ነው። ባዙቃውን ተሸክሞ ወደ ላይ ሲመለከት፣ በስር ከዋሻ ብቅ ብሎ አንዱ ይጠለዋል።
አራተኛ አሁን ያለው ሠራዊት በስሜት የሚዋጋ ሠራዊት አይደለም። የሚለግም፣ በህዝቡ ላይ መተኮስ የማይፈለግ፣ እያጉረመረመ ያለ ሠራዊት ነው። በአለቆቹ እየተሰደበ፣ የዘር ልዩነት እየተደረገበት፣ እድገትና የውጭ ስልጠና ለአንድ ብሔረሰብ ተወላጆች ብቻ ስለሚሰጠት የተማረረ ሠራዊት ነው። እንዲህ አይነት ሠራዊት ተዋግቶ ድል ማድረግ አይደለም፣ አንድ እርምጃ መራመድ አይችልም።
አምስተኛ ቀውስና አለመረጋጋት የተፈጠረባቸው ቦታዎች አድማሳቸው በጣም የሰፋ ነው። ድፍን ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር (ጎንደር ከተማ፣ ዳባት፣ ደባርቅ፣ አምባ ጊዮርጊስ፣ አዘዞ፣ ማክስኚት፣ ጎርጎራ፣ አርማጭሆ፣ ዳንሻ፣ ደብረ ታቦር፣ ጋይንት፣ አዲስ ዘመን፣ አዘዞ፣ ጭዋሂት፣ ሐሙሲት፣ ሳቆጥራ፣ አለፋ፣ አይንጋ፣ ሳንጃ፣ ሙሴ ባንድ፣ ቆላ ደባ …) በምእራብ ጎጃም ዞን (ፍኖት ሰላም፣ ማንኩሳ፣ ቡሬ፣ ጅጋና እንዳለ የዳሞት አወራጃ)፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን (ደብረ ማርቆስ፣ አባይ በረሃ ፣ በደጀን አርጎ ወደ ሞጣ ከዚያ ባህር ዳር በሚወስደው መንገድ በአይንጋ)፣ በባህር ዳር ከተማ እና በጢስ አባይ ከተማ፣ በሰሜን ወሎ ሸዋ (መቄት፣ ቆቦ፣ ማጀቴ …)፣ በአጠቃላይ በመላው የአማራ ክልል ማለት ይቻላል እንቅስቃሴና ተቃውሞ አለ። በስንቱ ቦታ ወታደር፣ ከዚህ እዚያ እያመላለሱ ይችላሉ? እንደ ደሴ፣ ደብረ ብርሃን፣ ወልዲያ፣ ኮምቦልቻ፣ ሸዋ ሮቢት ባሉ ቦታዎች ህዝቡ ተቃውሞ ለማሰማት ተዘጋጅቷል። በነዚህ ከተሞች ከፍተኛ የወታደር ክምችት አለ። ህዝቡ እንዳይወጣ ለማፈን እየተጠባበቀ ያለ። ወታደሮቹ ወደ ሌላ ቦታ ከተንቀሳቀሱ ሸዋና ወሎ እንደ ፍም እሳት መቀጣጠሉ አይቀሬ ነው።
እስከ አሁን በተደረገው መለስተኛ ጦርነት፣ ህወሓቶች ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን አፍነው ለመወሰድ ብዙ ጊዜ ሞክረው አልተሳካላቸውም። ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀመሮ እስከ አሁን በሰሜን ጎንደር ዞን ብቻ (ጎጃምን እና ደቡብ ጎንደር ዞንን ሳይጨምር) ቢያንስ 145 ወታደሮች ሕይወታቸው ጠፍቷል።
በጎንደር ከተማ አሥራ ስድስት የፌዴራል ፖሊስ፣ አንድ የመከላከያ ሠራዊት፣ አንድ ሚሊሺያ፣ ስምንት ልዩ ኃይል የተገደሉ ሲሆን በአዘዞ ሦስት፣ በአይንጋ አሥራ ሦስት፣ በአምባ ጊዮርጊስ ሦስት፣ ቆላድባና አዘዞ መሃል ላይ (ከገበሬ ማኅበር ጋር በተደረገ ጦርነት) ዘጠኝ፣ በሙሴ ባንድ ዘጠና አንድ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተገድለዋል።
በአጠቃላይ 143 ወታደሮች። (ይህ መረጃ የተገኘው በሰሜን ጎንደር በጸጥታና ደህነነት እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት አመራር አባላትን ባካተተ ስብስባ ከቀረበ ሪፖርት ነው)
አንድ መቶ አርባ አምስት ወታደሮች መገደላቸው፣ የህወሓት ጦር ያለበትን ከፍተኛ አጣብቂኝ አንዱን ገጸታ ብቻ ነው የሚያሳየው። ትጥቃቸውን እየያዙ ሠራዊቱን ትተው፣ ህዝቡን ከቀድሞ አለቆቻቸው ለመጠበቅ የህዝቡን ትግል የተቀላቀሉም ጥቂት አይደሉም። አዘዞ ከሚገኘው የጦር ካምፕ ብቻ ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ትላንት 13 የሠራዊቱን አባል ያካተተ አንድ ጋንታን ጨመሮ፣ አንድ መቶ አርባ አንድ ወታደሮች ካምፑን ጥለው ሄደዋል። ጠፍተዋል።
የህዝብን መብት በኃይልና በጠመንጃ ማፈን አይቻልም። ህዝብ ቆርጧል። የህወሓትን መንግሥት በፊትም አልመረጥኩም፣ አሁንም እኔን አይወክልም። ይሄን መንግሥት የምሸከምበት ትከሻ ከአሁን በኋላ የለኝም ብሏል።ይህ ህዝብ አንገቱን ከዚህ በኋላ አይደፋም። የዚህን ህዝብ ጥያቄ ከመስማትና ከማክበር ውጭ ሌላ አማራጭ የለም። የዚህ ህዝብ ጥያቄ ፍትህ፣ ሰላም፣ ልማት፣ እኩልነት፣ አንድነት፣ ዲሞክራሲ ነው።
በመሆኑ የህወሓት መንግሥት ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ ነገሮች የበለጠ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት፣ ነገሮችን በማርገብ፣ ራሱን ለብሔራዊ እርቅ እንዲያዘጋጅ አሳስባለሁ። በአፋጣኝ የሚከተሉት ቢደረጉም ይጠቅማሉ ብዬ አስባለሁ።
1. የሕሊና እስረኞች በሙሉ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ
2. የሽግግር መንግሥት ወይንም ካቢኔው አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎችን ያካተተ (መድረክ፣ ሰማያዊ፣ መኢአድ. የቀድሞ አንድነትና ኢዴፓ) የአንድነት መንግሥት ይቋቋም (ጦርነት ወይንም ችግር ሲፈጠር ብዙ ጊዜ እስራኤሎች የፓርቲ ልዩነቶቻቸው ወደ ጎን አድርገው ለአገራቸው ደህነንት ሲሉ የአንድነት መንግሥት ይመሰርታሉ) ከእስራኤሎች ትምህርት ይወሰድ። ከፓርቲ ይልቅ የሀገር ሰላምና ደህንነት ይቅደም።
3. አሁን ያለውን የፌዴራል አወቃቀር የሚመረመር ገለልተኛ ኮሚሽን ይቋቋም። ይሄ በዘር ላይ የተመሰረተው ፌዴራል አወቃቀር ነውና አሁን ወዳለነብት ቀውስ ውስጥ የከተተን።
4. ፖሊሲ፣ ፍርድ ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ የህዝብ ቆጠራ ጽ/ቤት፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ ሜዲያው ነጻና ገለልተኛ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚረዳ ተቃዋሚዎችና ባለሞያተኞችን ያካተተ ኮሚሽን ይቋቋም።
5. ለሁለት ዓመት በኋላ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይደረግ።