አይሻ መሐመድ

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂንየር አይሻ መሐመድ

ሱር ኮንስትራክሽን፣ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን፣ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን በዋቢነት ይጠቀሳሉ

ኢዛ (እሁድ ግንቦት ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 16, 2021)፦ ባለፉት ሁለት ዓመታት የግንባታ ሥራዎቻቸው የተስተጓጐለ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታዎችን፤ ሥራውን ወስደው በነበሩ ኮንትራክተሮች ማስቀጠል ባለመቻሉ በመንግሥት የኮንስትራክሽን ድርጅቶች እንዲሠሩ ስለመወሰኑ ተሰማ።

በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ግንባታቸውን በአግባቡ ባለማከናወናቸውና አሁን ግንባታቸው የተስተጓጐሉና ሥራውን ተረክበው በነበሩ ኮንትራክተሮች ለመቀጠል ያልተቻለው ግንባታውን የመቀጠል አቅም በማጣታቸውና የአንዳንዶቹም የኮንስትራክሽን ባለቤቶች አገር ለቀው በመውጣታቸው መኾኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

እነዚህ ኮንትራክተሮች ቀድሞም ቢኾን ከአቅም በላይ ተደራራቢ ሥራዎች የተሰጣቸው በመኾኑ፤ በእጃቸው ያለውን ሥራ በአግባቡ ማጠናቀቅ ብቻ ሳይኾን የአንዳንድ ፕሮጀክቶችን ሥራ ቅድሚያ ክፍያ ተቀብለው ግንባታውን ያልጀመሩ እንደነበረ ገልጸዋል።

እንደ ምንጮቻችን ገለጻ፤ በእጃቸው በብዙ ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ፕሮጀክቶች ተቀብለው በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙትን ግንባታዎች በማቆማቸው የሥራ ውላቸው እንዲቋረጥ ተደርጐ፤ በመንግሥት የኮንስትራክሽን ድርጅቶች እንዲገነቡ ይደረጋል ከተባሉት ውስጥ የመንገድና የተለያዩ ማኅበራዊ ግልጋሎቶች የሕንፃ ግንባታዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ። ከዚህም ሌላ በአንዳንድ የክልል ከተሞች ያሉ የኤርፖርት ግንባታዎች፣ የጤና ተቋማትም ይገኙበታል።

በመቶ ቢሊዮን ብር የሚገመት ዋጋ ያላቸው የእነዚህ ፕሮጀክቶችን ሥራዎች አቋርጠዋል ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ ሱር ኮንስትራክሽን፣ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን፣ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን በዋቢነት ይጠቀሳሉ።

ሌሎቹ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎችም መጠኑ እነዚህ ሦስት ኮንትራክተሮች ወስደዋል ተብሎ ከሚገመተው የፕሮጀክቶቹ ቁጥር አንጻር ሲታይ አነስተኛ ቢኾንም፤ በተመሳሳይ ችግር የግንባታ ውላቸው ተቋርጦ ሥራው ለመንግሥት የግንባታ ተቋማት የሚተላለፍ ስለመኾኑም የእነዚሁ ምንጮች ገለጻ ያመለክታል።

ከለውጡ በፊት ተደራራቢ ሥራዎችን በመውሰድ የሚጠቀሱ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች በእጃቸው ከ15 – 40 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ፕሮጀክቶችን ተረክበው ሲሠሩ የቆዩ ናቸው።

ሰሞኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂንየር አይሻ መሐመድ እንዳመለከቱት ግንባታቸው የቆሙ የፕሮጀክቶችን በኮንስትራክተሮቹ ማስቀጠል እንደማይችል በመታወቁ፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በተሰማሩ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለማሠራት መታቀዱን ለፓርላማው ሪፖርት ባቀረቡ ወቅት መግለጻቸው ይህንኑ ያመላከተ እንደኾነ ታውቋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ እነዚህ ግንባታቸው ከቆሙ አንዳንዶቹን ፕሮጀክቶች ለሌላ ኮንትራክተሮች ለመስጠት የወጡ ጨረታዎች ባለመሳካታቸው መንግሥት በራሱ አቅም ለማሠራት ያስገደደው ስለመኾኑም ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች በዚህ መልክ ግንባታቸው እንዲቋረጥ ማድረጉ አገሪቱ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍላት እንደኾነ የተጠቆመ ሲሆን፣ በተለይ ግንባታው ከተቋረጠ በኋላ በድጋሚ ማስጀመሩ ደግሞ ፕሮጀክቱ መጀመሪያ ከተያዘላቸው በጀት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር የሚከናወን ይኾናል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ