አሳሳቢው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ
የገቢዎች ሚኒስቴር
በአንድ ሳምንት ከ69 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ሥር ዋለ
41 ተሽከርካሪዎች ኮንትሮባንድ ጭነው ተይዘዋል
ኢዛ (ሰኞ ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 17, 2021)፦ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የጦር መሣሪያዎች እና የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዳስታወቀው ከሚያዝያ 25 ቀን እስከ ግንቦት 6 ቀን ድረስ የተያዙት እነዚህ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የጦር መሣሪያዎች፣ የተለያዩ አልባሳት፣ ምግብ ነክ ምርቶች፣ የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች፣ የመዋቢያ ዕቃዎች ልባሽ ጨርቆችና ጫማዎች ይገኙበታል።
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የተለያዩ መድሃኒቶች፣ አደንዛዥ ዕፅና የመሳሰሉት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የተያዙት በአዲስ አበባ ኤርፖርትና እንደ ጅጅጋ፣ ሐዋሳ፣ ኮምቦልቻና ሌሎች የጉምሩክ ጣቢያዎች ነው።
በገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ከተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ ግምታቸው 66.74 ሚሊዮን ብር የሚኾነው ወደ አገር ሲገቡ የተያዙ ናቸው። 2.47 ሚሊዮን ብር ያላቸው ደግሞ ከአገር ሊወጣ ሲል የተያዘ ነው።
በተከታይ ከሚወጡ መረጃዎች የኮንትሮቦንድ እንቅስቃሴው አሁንም ለአገር ራስ ምታት ኾኖ የቀጠለ ስለመኾኑን የሚያመለክት ሲሆን፤ በገቢዎች የሚኒስቴር የዛሬ መረጃ ላይም በአዲስ አበባ ኤርፖርት፣ በሞያሌና በድሬ ዳዋ ከፍተኛ የኾነ የገቢ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የታየ መኾኑን ጠቅሶ፤ 41 ተሽከርካሪዎች የኮንትሮባንድ ዕቃ ይዘው መያዛቸውንም ጠቅሷል። (ኢዛ)



