ባለፉት ሦስት ዓመታት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የአማራ ተወላጆች መፈናቀላቸው ተገለጸ
ዶ/ር ፈንቱ ማንደፍሮ፤ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር
ከሰሜን ሸዋ፣ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ብቻ ከ300 ሺህ በላይ ተፈናቅለዋል
ችግሩ ባለፉት 30 ዓመታት የተዘራው ጥላቻና ችግሮችን በወቅቱ ማረም ባለመቻሉ መኾኑን ክልሉ አስታወቀ
ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ጥሪም ቀርቧል
ኢዛ (ሰኞ ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 17, 2021)፦ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተዘራው የጥላቻ ትርክትና ጥቃት ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ የአማራ ክልል ተወላጆች መፈናቀላቸውን የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል። ከሰሜን ሸዋ እና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳደር ብቻ ከ300 ሺህ በላይ ዜጐች መፈናቀላቸውም ታወቀ።
በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔር አስተዳደር በተፈጸሙ ጥቃቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችልና በክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን በተመለከተ በተሰጠ መግለጫ ነው።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፈንቱ ማንደፍሮ በተሰጠው የዛሬው መግለጫ መሠረት ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ፣ ከቤንሻንጉልና በአማራ ክልል በራሱ ክልሉን የኹከትና የግጭት ማዕከል ለማድረግ ታስቦ በተሠራ ሥራ ከ565 ሺህ በላይ ዜጐች መፈናቀላቸውን ነው።
እነዚህ ተፈናቃዮችም በክልሉ በሚገኙ 154 ወረዳዎች በተለዩ መጠለያዎችና ቤተዘመዶች ጋር ተጠልለው እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ይህም ክልሉ የተፈናቃዮችን የሚያስተናግድና የጥቃት ማዕከል እንዲኾን በማለትም አመልክተዋል። በቅርቡ በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሚያ ብሔረሰብ ልዩ ዞን አስተዳደር ኾን ተብሎ ታቅዶና ታልሞ በተፈጠሩ ግጭቶች ከ300 ሺህ በላይ የሚኾኑ ወገኖች ከቀያቸው ስለመፈናቀላቸውም ገልጸዋል።
እነዚህ ተፈናቃዮች በአሁኑ ወቅት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በመኾናቸው የኢትዮጵያ ሕዝብና ሌሎች ለጋሽ ተቋማት ክረምቱ ከመግባቱ በፊት መጠለያ ለማኖር እገዛ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የዕለቱ ዋነኛ መግለጫቸው ለእነዚህ ተፈናቃይ ወገኖች ዜጐች እጃቸው እንዲዘረጉ ጥሪ ማስተላለፍ ቢኾንም ለእነዚህ ዜጐች መፈናቀልና መጠቃት ዋነኛ ምክንያት ነው ያሉት የጥላቻ ትርክት ስለመኾኑ አጽንኦት ሰጥተው የገለጹበት ነው።
እንዲህ ያለው የጥላቻ ትርክትና ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ዛሬ በአማራ ተወላጆች ላይ ይታይ እንጂ ችግሩ ከክልል አልፎ ለአገር አደጋ መኾኑንም አመላክተዋል።
ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በአገራችን የተዘራው የጥላቻ ዘር ፍሬው አፍርቶ አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ዜጐቻችን በተለይ የአማራ ክልል ሕዝብ የጥቃት ማዕከል በየቦታው የአማራ ሕዝብ ተወላጆች የኾኑበት አካባቢ ሁሉ የጥቃት ዓላማ እንዲኾኑ ተደርገዋልም በማለት ያስታወቁት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዜጐቻችን ያለምንም ምክንያት በገዛ አገራቸው የሞት፣ የስደት፣ የመፈናቀል ሰለባ ኾነዋል።
ይህንን ሁኔታ እንደ አገር በጋራ መመከት እንደሚገባና በጋራ ካላስቆምነው በአንድ ክልል ብቻ የሚደረግ መኾን የለበትም።
“ነባራዊ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩን ችግሮች እየሰፉ ሔደው የክልል ዕዳ ከመኾን አልፈው የአገር ዕዳ መኾናቸው አይቀሬ ነው” በማለት፤ አሁን ያለውን ሁኔታ በጋራ በመቆም መመከት አለብንም ብለዋል። ይህንንም የሌሎች አገሮች ገጠመኞችን በመጥቀስ አስረድተዋል። “ብዙ አገሮች ሳያስቡት እንደ አገር የመቀጠል ችግር የገጠማቸው በትንሽ አካባቢ የተፈጠሩ ክስተቶችን በወቅቱ ማረም ባለመቻላቸው ነው፤ በአንድ አካባቢ የተከሰተውን ችግር የእኛም ችግር ነው ብለው ለችግረኞችና ለተጐጂዎች በጋራ መጮህ ባለመቻላቸው እንደኾነ በመጥቀስ፤ ይህ በመኾኑ መጨረሻ ላይ እሳት መርጦ አያቃጥልምና በአገሪቱ ውስጥ የነደደው እሳት ሁሉንም አቃጥሏል።” በማለት የአንዱ ጉዳት ሌላው ተሰምቶት የእኔም ጉዳት ነው ያለ ማለት አደጋው የከፋ መኾኑን አስገንዝበዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን በተለመደ የአንድነት ሥነ ልቦና ቆመን ዛሬ በዚህ ክልልና በየቦታው በክልሉ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን መፈናቀል በጋራ ይበቃል ልንል ይገባል በማለት መልእክታቸው በክልሉ መንግሥት ስም አስተላልፈዋል። በክልሉ አሁን እርዳታ በማሰባሰብ ተጐጂዎችን ለመደገፍ የታሰበበትን መንገድና እርዳታው እንዴት እንደሚሰጥም በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል። ምክትል መስተዳደሩ የሰጡት መግለጫ የሚከተለው ነው። ለማየትና ለማዳመጥ የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ! (ኢዛ)



