የአሜሪካ አቋምና የኢትዮጵያ ምላሽ
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ጀፍሪ ፊልትማን
የውጭ ጣልቃ ገብነት ያየለበት ወቅት ኾኗል
ኢዛ (ረቡዕ ግንቦት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 19, 2021)፦ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ እያራመደ ያለው ጣልቃ ገብነት እየጠነከረ መምጣቱንና ይህንን በመቃወም የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫዎችን ከማውጣት ጀምሮ ቅዋሜውን ለመግለጽ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው።
በቅርቡ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ለመጐብኘት የመጡት የአሜሪካው ልዩ መልእክተኛ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ለኮንግረስ ያቀረቡት ሪፖርት የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸውና በተለይም በትግራይ ክልል አሉ ያሉትን የአማራ ልዩ ኃይልና የኤርትራ ሠራዊት እንዲወጣ የጠየቁበትም ነበር።
ከዚህም ሌላ ከሕወሓት ቡድን ጋር ድርድር ይደረግ የሚልም ግፊት የያዘው የአሜሪካ አቋም፤ በኢትዮጵያ ዘንድ ፈጽሞ የተወደደ አልኾነም። ይህ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በተመለከተ ትናንትና ዛሬ የወጡ መግለጫዎች ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የምትቃወም መኾኗንና በጉዳዬ ውስጥ አትግቡብኝ የሚል መልእክት የያዘ ነው።
የውጭ ጣልቃ ገብነትንና አንዳንድ ሚዲያዎች እያራገቡ ያሉትን ዘገባ በእጅጉ የኮነነ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጠው መግለጫ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር በመኾኗ በውስጧ ጉዳይ ላይ ከውጭ ምንም መመሪያ እንደማትቀበል በይፋ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠር ላይ ያተኮሩ ፍትሐዊ ያልኾኑ ዘመቻዎች እየተካሔዱ እንደሚገኙ ያመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት አጋር አካላት ለሚያሳስባቸው ጉዳዮች አዎንታዊ ምላሽ እየሰጠ ቢኾንም፤ አንዳንድ አካላት ከውንጀላ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ያለመቻላቸውም አስታውሷል።
አንዳንድ የኢትዮጵያ አጋሮች ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ችግሮች ለመላቀቅ የምታደርጋቸው ጥረቶች ከመረዳትና ከመደገፍ ይልቅ፤ ሁኔታውን ማባባስ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውንም በማመልከት፤ ይህ በመኾኑ ኢትዮጵያ በድጋሚ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አቋሟን ግልጽ ለማድረግ መገደዷንም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
በተለይ የትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም ማኅበረሰብ ጋር ለመሥራት ቁርጠኝነቱን መግለጹ ብቻ ሳይኾን፤ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪዎች ያለ ምንም ገደብ በክልሉ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ማድረጉን፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ድጋፍ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን፤ ችግሩ አሁን እንደተፈታ ጭምር በማመልከት በእነዚህ ሁኔታዎች የተዛቡ ዘገባዎችም ተቀባይነት የላቸውም ብሏል።
የሰብአዊ መብት ጥሰት ክሶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ቁርጠኝነቱን እንደገለጸ፤ እንዲሁም ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮችን ያቀፈ ቡድን በትግራይ ክልል ተሰማርቶ የምርመራውን ሥራ እየሠራ መኾኑንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር እየሠራ መኾኑን እንዲሁም ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ግልጽ፣ እና ተአማኒ በኾነ መልኩ በማድረግ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ነፃነትና ዴሞክራሲ እንዲኖር ለማድረግ በመሠራት ላይ ያለውን ሥራም በመግለጫው ላይ አስፍሯል።
በተለይ ከአሜሪካ መንግሥት እየቀረበ ያለውን የአማራ የጸጥታ ኃይል ከትግራይ ክልል ይውጣ የሚለውን ጥያቄ በዚህ መግለጫው በብርቱ ኮንኗል። ይህንንም የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የጸጥታ ኃይሉን ያለ ምንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ በየትኛውም ስፍራ ማሰማራት እንደሚችል በመጥቀስ፤ አሜሪካ የያዘችውን አቋም ኮንኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ተቋማት እና አንዳንድ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ተጽዕኖ በመቃወም ሰልፍ አካሒደል።
አንዳንድ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ያልተገባ ጫና እንዲያቆሙ እና በአሸባሪው የሕወሓት ደጋፊዎች የሚነዛውን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ተመርኩዘው በየጊዜው ከሚያወጡት የተዛባ መግለጫ እንዲቆጠቡ የጠየቀም ነበር።
በተለይም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኢትዮጵያ ላይ ያወጣው መግለጫ የአገራቱን የቆየ ወዳጅነት ያላገናዘበ፣ በሐሰት መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ ግፊት የወጣ መኾኑን በመግለጽ መግለጫውን የተቃወሙ ሲሆን፤ ከዚህ ድርጊታቸው ይቆጠቡልን በማለት ሰልፈኞቹም ጠይቀዋል። (ኢዛ)



