ዐረብ ሊግና የተንሻፈፈው አቋሙ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ
በህዳሴ ግድብ ላይ ሊጉ የያዘው አቋም በኢትዮጵያ ተቃውሞ ቀርቦበታል
ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 16, 2021)፦ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ አቋም በተፃራሪ ይዘት ያለውን መግለጫ ያወጣው የዐረብ ሊግ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞ ቀርቦበታል።
የዐረብ ሊግ አባል አገራት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብጽ እና ከሱዳን ወግነው ያወጡት መግለጫ አስመልክቶ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የሊጉ መግለጫ ወገናዊነት ያለበት መኾኑን በመንቀፍ፤ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ የመጠቀም መብቷን የሚፃረር በመኾኑ በማመልከት፤ የአባል አገራቱ መግለጫ ተገቢነት የሌለው መኾኑን በይፋ አስታውቋል።
በተለይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ፤ ተቀባይነት የሌለውና ሚዛናዊነት የጐደለው በማለት የዐረብ ሊግን መግለጫ ኮንነዋል።
ሊጉ የግብጽ እና የሱዳንን ቅሬታ ተቀብሎ ያሳለፈው ውሳኔ፤ የህዳሴውን ግድብ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ አንደምታ እንዲኖረው በማድረግ፣ የዓባይን ወንዝ በትብብር እና በዘላቂነት ለመጠቀም የማያስችል ነው በማለት ሊጉ ያወጣውን መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የማትቀበለው እና ሚዛናዊ አለመኾኑን በዚሁ ጉዳይ ላይ የወጣው የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ አመላክቷል።
የህዳሴውን ግድብ የውኃ ሙሌት በተመለከተ ሊጉ የያዘውንም አቋም የሚተቸው የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ፤ “የውኃ ሙሌቱ ስምምነት ሳይደረግበት ተፈጻሚ እንዳይኾን” የሚለውን የሊጉን አቋም፤ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የማትቀበለው ስለመኾኑም አመልክቷል።
በአጠቃላይ ሊጉ እንዲህ ያለውን መግለጫ ከማውጣት ይልቅ፤ ሦስቱንም የተፋሰስ አገሮች ተጠቃሚ የማያደርግ ውሳኔ ቢያሳልፍ ይሻል እንደነበር በማመልከት፤ ሊጉ ይህንን አቋሙን መልሶ ያየዋል የሚል እምነት እንዳለውም የኢትዮጵያ መንግሥት በዛሬው መግለጫ አስገንዝቧል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የውኃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ በማከናወኑ ላይ የማያወላውል አቋሟን በተደጋጋሚ የገለጸች ቢኾንም፤ የዐረብ ሊግ አባላት ጉዳዩን ወደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመውሰድ፤ የውኃ ሙሌቱ እንዳይካሔድ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን ማለታቸው ተሰምቷል።
የዐረብ ሊግ ፈጽሞ ተቀባይነት መግለጫ ያወጣው በኳታር በህዳሴ ግድብ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ ነው። (ኢዛ)



