Takele Uma, Minister for Mines, Petroleum and Natural Gas of Ethiopia

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማ

በቀጣዩ ዓመት ከማዕድን ዘርፍ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ታቅዷል
የጸጥታ ችግር እንዲፈታ ተጠይቋል

ኢዛ (እሁድ ሰኔ ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 27, 2021)፦ ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፍ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ባለፉት ሁለት ዓመታት መሻሻል የታየበት ሲሆን፣ በሚቀጥለው በጀት ዓመትም ከ1.5 (ከአንድ ነጥብ አምስት) ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት እቅድ መያዙንና ባለፉት 11 ወራትም ከ668 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ በአሁኑ ወቅት ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እየጨመረ መኾኑንና በቀጣይ ዓመትም ከዚህ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ያስችላሉ የተባሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ዛሬ እሁድ ሰኔ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረጉት መረጃም በቀጣይ ዓመት የታቀደውን የ1.5 ቢሊዮን ብር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ይቻል ዘንድ ከክልሎች ጋር መግባባታቸውን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፍ የምታገኘው ገቢ እየጨመረ መምጣቱ በ2013 በጀት ዓመት ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ዘርፍ ሊኾን አስችሎታል።

ወቅታዊ አኀዛዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከማዕድን ዘርፍ በ11 ወሮች የተገኘው ገቢ ከ2012 በጀት ዓመት ጋር እንኳን ሲነጻጸር ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ ያለው ኾኗል። በአንድ ዓመት ልዩነት ዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢውን በዚህ ደረጃ ያሳደገ የወጪ ንግድ ምርት ያለመኖሩ፤ ዘርፉ ተስፋ የተጣለበት እንዲኾን አድርጎታል። ዘንድሮ በአሥራ አንድ ወር ውስጥ አገሪቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ3.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘቷን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያሳወቀ ሲሆን፤ ይህ ገቢ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓመት ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከውጭ ምንዛሪ ገቢ ያገኘችበት ሊኾን ችሏል።

ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ታሪኳ ሦስት ቢሊዮን ዶላር የደረሰችበት ወቅት ያልነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በዓመቱ ውስጥ ያገኘችው 2.9 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ይታወሳል።

በ2013 በጀት ዓመት የተገኘው 3.2 ቢሊዮን ዶላር በ11 ወር የተገኘ በመኾኑ የሰኔ ወር ገቢ ሲታከል የዘንድሮ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ወደ 3.5 ቢሊዮን ብር ሊጠጋ ይችላል የሚል እምነት አሳድሯል። ለዚህም ገቢ እድገት የማዕድን ዘርፍ ላይ የታየው ለውጥ ነው።

ከአኀዛዊ መረጃዎችና ከተያዘው እቅድ አንጻር በ2014 በጀት ዓመት ከዘርፉ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገኝ ከኾነ፤ ኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዋነኛ መገኛ ኾኖ የቆየውን ቡና በመብለጥ የማዕድን ዘርፍን ቀዳሚው የውጭ ምንዛሪ መገኛ ያደርገዋል።

እስካሁን ከአገሪቱ የወጪ ንግድ ምርቶች ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚኾነውን ወይም በየዓመቱ ከ600 – 800 ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኘው የቡና የወጪ ንግድ ሲሆን፤ አሁን ባለው አካሔድ ግን የማዕድን ዘርፍ ብልጫውን ሊወስድ ይችላል እየተባለ ነው።

ቡና የአገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ መገኛ ኾኖ የቆየ ቢኾንም፤ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዲያስገኝ በየዓመቱ የሚታቀድ ቢኾንም፤ እስካሁን 800 ሚሊዮን ዶላር እንኳን መድረስ ሳይችል ቀርቷል።

ከዚህ አንጻር ትልቅ ለውጥ የታየበት የማዕድን ዘርፍ በእቅዱ ከሔደ ቡና ቦታውን ለማዕድን ዘርፍ ያስረክባል።

ከማዕድን ዘርፍ ደግሞ ከፍተኛውን ገቢ እያስገኘ ያለው ወርቅ መኾኑም ታውቋል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ይህንን ውጥኑን ዳር ለማድረስ ግን በማዕድን ማምረቻ አካባቢዎች ያሉ የጸጥታ ችግሮችን መፍታት ግድ መኾኑ ተጠቁሟል።

በዛሬው ዕለትም የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ የመከረ ሲሆን፤ ሰላም ሚኒስቴር በማዕድን ማውጫ አካባቢዎች የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን በተመለከተ በሰላም ሚኒስቴር በኩል መፍትሔ የሚያገኝ መኾኑን መግባባት ላይ ደርሰናል በማለት ኢንጂነር ታከለ ገልጸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ