ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጋር ስብሰባ ሲያካሒዱ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከካቢኔ አባላቶቻቸው ጋር ስብሰባ ሲያካሒዱ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ1.13 ቢሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን አጸደቀ

ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 30, 2021)፦ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር በተደረጉ ስምምነቶች መሠረተ ከ1.13 (አንድ ነጥብ አንድ ሦስት) ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር ለማግኘት የሚያስችሉ አራት ስምምነቶችን የያዙ ረቂቅ አዋጆችን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሔደው 99ኛ መደበኛ ስብሰባ በአራት የብድር ስምምነቶች ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ፤ አዋጆቹ እንዲጸድቁ በሙሉ ድምፅ ወደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፏል።

ይህ የ1.13 ቢሊዮን ዶላር አሁን ባለው የምንዛሪ ዋጋ 50 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሲሆን፤ ለአራት ለተለያዩ ክንዋኔዎችና ፕሮጀክቶች የሚውሉት እነዚሁ ብድሮች ምንም ዐይነት ወለድ የማይታሰብባቸው መኾኑም ተገልጿል። ባንኩ (ዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር) ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚሰጠው አገልግሎት 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚታሰብባቸው ሲሆን፤ የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ያካተቱ ከመኾኑም በላይ ብድሮቹ በ38 ዓመታት የሚከፈሉ ናቸው።

ምክር ቤቱ እነዚህ ብድሮች ለምን ለምን ተግባራት ማስፈጸሚያ እንደሚውሉ በዝርዝር የሚያሳየውን እና በሌሎች ረቂቆች ላይ ውሳኔ ያሳለፈበት ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባላት ከዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጋር ስብሰባ ሲያካሒዱ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ አባላት ከዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጋር ስብሰባ ሲያካሒዱ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ99ኛ መደበኛ ስብሰባ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ሁለት ጉዳዮች

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር በተደረጉ በአራት የብድር ስምምነቶች ላይ ተወያይቷል። የመጀመሪያው የብድር ስምምነት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ያለውን ተደራሽነት የማሻሻል እና ለገጠሩ ሕብረተሰብ በቤተሰብ ደረጃ፣ ለማኅበራዊ ተቋማት እንዲሁም ለኢንተርፕራይዞች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማሳደግ የሚውል ነው። ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውለው ብድር 500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው።

ሁለተኛው የብድር ስምምነት ዓላማ የመሠረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ ማሻሻልና የተጠያቂነት ሥርዓትን ማጠናከር ሲሆን፣ በወረዳ ደረጃ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የውኃ እና የገጠር መንገድ አቅርቦት መሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግና የአገራችንን ያልተማከለ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ለማጠናከር የሚያግዝ ነው። የብድር መጠኑም 250 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው።

ሦስተኛው የብድር ስምምነት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አማካኝነት የሚተገበር አነስተኛ እና መካከለኛ እንተርፕራይዞችን በፋይናንስ ለማጠናከር ለመደገፍ የሚውል ሲሆን፤ የብድር መጠኑም 180 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው።

አራተኛው የብድር ስምምነት የመረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂ በማዘመን ኢኮኖሚውን እና አጠቃላይ የመንግሥት አሠራርን ከተለመደው ባህላዊ የአሠራር ዘዴ ወደ ዲጂታል የመቀየር ሥራዎችን ለማስፈጸም የሚውል ሲሆን፤ የብድር መጠኑን 200 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። በድምሩ የ1 ቢሊየን 130 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የብድር ስምምነቶች በማጽደቂ ረቂቅ አዋጆች ተደግፈው ቀርበዋል። ሁሉም ብድሮች ምንም ዐይነት ወለድ የማይታሰብባቸው፤ ባንኩ ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚሰጠው አገልግሎት 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚታሰብባቸው ኾነው የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው። ምክር ቤቱም ከአገራችን የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ እና ምንም ዐይነት ተጓዳኝ ጫና የሌላቸው መኾኑን በማረጋገጥ በሙሉ ድምፅ በማጽደቅ ረቂቅ አዋጆቹ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል።

2. ምክር ቤቱ በመቀጠል የተወያየው የአፍሪካ የመንገድ ደኅንነት ቻርተር እና የተባበሩት መንግሥታት የመንገድ ትራፊክ ኮንቬንሽን ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው። የነዚህ ሁለት ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች መጽደቅ አገራችን በመንገድ ትራንስፖርት ረገድ ከጎረቤት አገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የሚያሳልጥ ከመኾኑም በላይ ብሔራዊ፣ አካባቢያዊና አህጉራዊ የመንገድ ደኅንነት ፕሮግራሞችን በቅንጅት ለመፈጸም የሚያስችል እንዲሁም በአገር ደረጃ ሰፊና ሁሉን አቀፍ የኾኑ የመንገድ ደኅንነት ፖሊሲዎች እንዲቀረጹ የሚያስችል መኾኑ ታምኖበት ለምክር ቤቱ ይሁንታ ቀርቧል። ምክር ቤቱም በጥልቀት ከተወያያ በኋላ በሙሉ ድምፅ በማጽደቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ