መንገድ ተዘግቷል
 
		የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከዚህ በኋላ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት የመሔድ እድል እንደሌለው ተገለጸ
ኢዛ (ዓርብ ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 9, 2021)፦ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከዚህ በኋላ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ሔዶ አጀንዳ የሚሔድበት እድል እንደሌለ ኢትዮጵያ አስታወቀች።
ዛሬ ዓርብ ሐምሌ 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋድ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ፤ በትናንትናው ዕለት የጸጥታው ምክር ቤት በግድቡ ዙሪያ ተወያይቶ የግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት በኩል መካሔድ አለበት የሚልና ጉዳዩ የልማት አጀንዳ መኾኑን መወሰኑን ገልጸዋል። በመኾኑም የግድቡ ጉዳይ ከዚህ በኋላ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት የሚሔድበትና አጀንዳ የሚኾንበት መንገድ ተዘግቷል በማለትም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
15ቱ የጸጥታው ምክር ቤት አባላት የተለያየ ሐሳብ ቢኖራቸውም፤ ሁሉም የግድቡ ጉዳይ የልማት እንጂ የጸጥታ ጉዳይ አለመኾኑን የተስማሙበት መኾኑን ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል መገኾኑንም አስታውቀዋል። የትናንቱ ውይይትም አስደሳች ውጤት እንዳስገኘ በሚመለከትም በትናንትናው ዕለት በተመድ ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን አቋም በማንጸባረቅ ላደረጉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል። (ኢዛ)



