በአገር ክህደት ከተፈረደባቸው የጦር መኮንኖች

በአገር ክህደት ከተፈረደባቸው የጦር መኮንኖች ሦስቱ (ፎቶ፣ ፋና)

እስከ 18 ዓመት ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል

ኢዛ (ሐሙስ ነኀሴ ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. August 26, 2021)፦ በአገርና በአገሪቱ ሠራዊት ላይ ክህደት በመፈጸም፣ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ጉዳያቸው በደቡብ ዕዝ ቀዳማዊ ጦር ፍርድ ቤት ሲታይ የነበሩ አሥር የጦር መኮንኖች እስከ 18 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወሰነ።

እነዚህ የእስር ቅጣት የተላለፈባቸው የጦር መኮንኖች ከአገር አፍራሽ አሸባሪዎች ጋር ምስጢራዊ ግንኙነት በመፍጠር፣ የአገር ደኅንነት ላይ አደጋ በመጣል የተከሰሱ ናቸው። ለቅጣት ያበቃቸው ተግባራቶቻቸው መካከል የአገር ክህደት በመፈጸማቸው፣ በአሸባሪነት የተፈረጁትን የሕወሓት ጁንታ ለመቀላቀል ማሴር፣ ለሸኔ ማቀበል፣ ከግዳጅ ቀጠና በመሸሽ የወገን ጦርን ለአደጋ ማጋለጥ፣ ያለበቂ ምክንያት ሲቪሎችን መግደል፣ … የሚሉ ይገኝባቸዋል።

ከዚህም ሌላ የበላይ ትእዛዝ ችላ በማለት ለንጹሐን ሞት ምክንያት መኾንና የመንግሥትንና የሕዝብን ወታደራዊ ንብረት ይዞ ለመሸሽ ሙከራ ማድረግ የሚሉ ክሶች ጭምር የቀረበባቸው ሲሆን፤ በእነዚህ ድርጊቶቻቸው ጥፋተኛ በመኾናቸው ከስምንት እስከ 18 ዓመት ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

ጉዳዩን የተመለከተው በደቡብ ዕዝ ቀዳማዊ ጦር ፍርድ ቤት፤ የእነዚህን ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ግራና ቀኝ የተመለከተ ሲሆን፤ ተጠርጣሪዎቹ ራሳቸውን መከላከል ባለመቻላቸው ተመጣጣኝ ያለውን ፍርድ ሊሰጥ ችሏል።

እንዲህ ባለው የአገር ክህደት የተጠረጠሩ 150 የሚኾኑ የጦር አባላትም ጉዳይ የፍርድ ሒደት የሚታይ መኾኑም ታውቋል።

ዛሬ ሐሙስ ነኀሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ውሳኔ የተላለፈባቸው 10 የጦር መኮንኖችና የተላለፈባቸው የቅጣት መጠን የሚከተለው ነው።

1. ሻለቃ ክፍሌ ካሳይ በ17 ዓመት ጽኑ እስራት፣
2. ኮሎኔል ክፍሌ ፍስሃዬ በ14 ከ2 ወር ጽኑ እስራት፣
3. ሀምሳ አለቃ መብራቱ ጥላዬ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት፣
4. መሠረታዊ ወታደር መኮንን ክንፈ በ13 ዓመት ጽኑ እስራት፣
5. ሀምሳ አለቃ ፈረደ ይባስ በ11 ዓመት እስራት፣
6. ምክትል አሥር አለቃ ሀጎስ በርሄ በ11 ዓመት ጽኑ እስራት፣
7. ምክትል ክፍሌ ንጉሥ በ9 ዓመት ጽኑ እስራት፣
8. ኮሎኔል ካሱ ሀብቱ በ11 ዓመት ከ2 ወር፣
9. ኮሎኔል ሀጎስ አሰፋ በ8 ዓመት ጽኑ እስራት እና
10. ሌተናል ኮሎኔል ሀይላይ ገብሩ በ10 ዓመት ከ2 ወር ጽኑ እስራት። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ