አንድነት ወደ አውሮፓ ነገ ይጓዛል
ወ/ት ብርቱካንና አቶ አክሉ ነገ ወደ ሎንዶን ይገባሉ
Ethiopia Zare (ኀሙስ ጥቅምት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. November 6, 2008)፦ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሁለት አመራሮቹን ነገ ወደ አውሮፓ ይሸኛል። አመራሮቹ በአውሮፓ ሰባት ሀገሮች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ የየሀገሮቹ ባለሥልጣናትና ከአውሮፓ ሕብረት ባለሥልኖች ጋር ለመወያየት ማቀዱን ለመረዳት ችለናል።
ፓርቲውን ወክለው ወደ አውሮፓ የሚበርሩት ሊቀመንበሯ ወ/ት ብርቱካን እና የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ አባልና የዕቅድና የስትራቴጂ ኃላፊ የሆኑት አቶ አክሉ ግርግሬ መሆናቸው ታውቋል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ያነጋገረው የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር፤ የፓርቲው የአውሮፓ ጉብኝት ከነገ ጥቅምት 28 (ኖቨምበር 7) ጀምሮ እስከ ኅዳር 21 (ኖቨምበር 30) ድረስ እንደሆነ ከሊቀመንበሯ ለመረዳት ችሏል።
ሁለቱ ልዑካኖች ነገ ከኢትዮጵያ ወደ እንግሊዝ ዋና ከተማ ሎንዶን የሚበሩ ሲሆን፣ ሥራቸውን የሚጀምሩትም በሎንዶን መሆኑን ለመረዳት ችለናል። በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት ሎንደን ውስጥ እስከ ኅዳር 2 (ኖቨምበር 11) ድረስ የሚቆዩ ሲሆን፣ በሎንደን ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ቅዳሜ ጥቅምት 30 (ኖቨምበር 9) ከሰዓት በኋላ ከ2 PM - 8 PM ድረስ ውይይት እንደሚያደርጉ ታውቋል።
የልዑካን ቡድኑ ከሎንዶን በተጨማሪ በብራስልስ (ቤልጅየም)፣ በስዊድን፣ በሆላንድ፣ በጀርመን፣ በስዊዘርላንድ እንዲሁም በኖርዌይ በተከታታይ የሥራ ጉብኝቱን እንደሚያካሂድ ለመረዳት ችለናል።