“ምን መሥራት እንዳለብኝ አልወሰንኩም” ዶ/ር ፍስኃ እሸቱ
Ethiopia Zare (እሁድ ኅዳር 21 ቀን 2001 ዓ.ም. November 30, 2008)፦ በቅርቡ የሙሉ ዩኒቨርሲትነት እውቅና ያገኘው የ”ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ” የቀድሞ ባለቤትና ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍስኃ እሸቱ፣ ሙሉ ንብረታቸውን በሽያጭ ለሼህ መሐመድ አሊ አል አሙዲና ለዶ/ር አረጋ ካስረከቡ በኋላ፣ በቀጣይ ስለሚሠማሩበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንዳላሰቡ ገለፁ። በቅርብ የሚያውቋቸው ምንጮች እንደጠቆሙት ላልተወሰነ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጭ ቆይታ እንደሚያደርጉ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ በግል ኮሌጅነት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዘው ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ፣ ባለቤትነቱ የዶ/ር ፍስኃ እሸቱ እና በወንድ ልጃቸው ተመዝግቦ ይገኝ የነበረ ሲሆን፣ ባለፉት አስር ዓመታት ቆይታው፣ ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን አስመርቋል። ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርስቲ ባደገበት በዚህ ዓመት መጀመሪያ በርካታ ተማሪዎችን የመዘገበ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 5 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች እንዳሉት ታውቋል።
የዩኒቨርስቲው ባለቤት ዶ/ር ፍስኃ እሸቱ፣ ለባለሀብቶቹ በሽያጭ ያስተላለፉት የኮሌጁ ንብረቶች፣ በአዳማ ከተማ የሚገኘውና በ18 ሺህ ሜትር ካሬ ላይ ያረፈውን “አዳማ ካምፓስ” ከነተማሪዎቹ፣ ገርጂ የሚገኘውና በ22 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው “ገርጂ ካምፓስ” ከነተማሪዎቹ፣ በገርጂ አካባቢ የሚገኘውና በ1 ሺህ 200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ባለ ስምንት ፎቅ ቢጫው ሕንፃና ግቢ ውስጥ የሚገኘው የተዘጋውና ኤ.ቢ.ቢ.አይ. የተባለው ጋዜጣ ይታተምበት የነበረው ማተሚያ ቤት ይገኙበታል።
ሽያጩ በተጠቀሱት ካምፓሶች ውስጥ ያሉትን ንብረቶች ተማሪዎቹንና ሠራተኞቹን በሙሉ ይጨምራል። ዶ/ር ፍስኃ እሸቱ የአክሲዮን ድርሻ ለመሸጥ ማስታወቂያ አውጥተው የነበረ ሲሆን፣ ይህን ሃሳባቸውን ቀይረው 80 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ለሼክ መሐመድ፣ 20 በመቶውን ደግሞ ለሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዶ/ር አረጋ ይርዳው በ66 ሚሊዮን ብር ሸጠዋል።
ዶ/ር ፍስኃ ለረጅም ዓመታት የለፉበትን፣ ንብረታቸውን ሙሉ ለሙሉ ለመሸጥ ያስወሰናቸውን ምክንያት ሲያብራሩ፤ በትምህርት ዘርፍ የተሠማራ ድርጅት በርካታ ሰዎችን በአክስዮን አቅፎ ለመሥራት እንደሚከብድ አስረድተዋል። በትምህርት ሥራ ዘርፍ ላይ ያለ ድርጅት፣ በርካታ ባለድርሻዎች ይዞ ቢቋቋም፣ ባለድርሻዎቹ በየዓመቱ ትርፍ ሊፈልጉ ይችላሉ። ዩኒቨርስቲውን ለማሳደግና ጥራት ያለው ሥራ ለመሥራት በነፃነት ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ትርፉ እንደ ባንክ፣ በየዓመቱ አትራፊ ባለመሆኑ ጭቅጭቅ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል የሚል ሥጋት ስለነበራቸው በደንብ አስበውበት ሙሉ ለሙሉ ለመሸጥ መወሰናቸውን ዶ/ር ፍስኃ ገልፀዋል።
በተጨማሪም “ሚድሮክ የገንዘብ ችግር ስለማይኖርበት፣ የትምህርት ተቋሙን በጥሩ ሁኔታ ያሳድገዋል” ያሉት ዶ/ር ፍስኃ በቀጣይ ለመሥራት ያሰቡትን የሥራ ዘርፍ ለቀረበላቸው ጥያቄ ”በአሁኑ ሰዓት ለመሥራት ያሰብኩት ምንም ነገር የለም፤ ለጊዜው ትንሽ ዕረፍት ማድረግ ያለብኝ ይመስለኛል” ብለዋል።
ለዶ/ር ፍስኃ ቅርብ የሆኑ ምንጮቻችን፣ ላልተወሰነ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጪ ቆይታ ለማድረግ እንዳሰቡ ጠቁመውናል።



