ዶ/ር ፍስኃ እሸቱ ለሁለተኛ ጊዜ ጋዜጣ በተኑ
ኤቢቢአይ ጋዜጣ መታተም አቆመ
Ethiopia Zare (እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. June 8, 2008)፦ የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት በሆኑት በዶ/ር ፍስኃ እሸቱ ባለቤትነት ስር በሚገኘው የሪሊያንስ አፍሪካ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ያሣትመው የነበረው ኤ.ቢ.ቢ.አይ. ዊክሊ የተሰኘው ሣምንታዊ ጋዜጣ መታተም አቆመ።
ባለፈው ሣምንት ድርጅቱ ለሠራተኞቹ በበተነው ደብዳቤ ላይ እንደገለጸው ለሠራተኞቹ ለአንድ ወር የሚቆይ የሥራ ማፈላለጊያ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።
ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ አፍሪካ ቤስትስ ቢዝነስ ኢንዴክስ /ኤ.ቢ.ቢ.አይ./ በሚል ስያሜ የማስታወቂያና የሕትመት ሥራ ድርጅት በማቋቋም አራት ጋዜጦችን (ኤ.ቢ.ቢ.አይ. ዊክሊ፣ ኤ.ቢ.ቢ.አይ. ስፖርት፣ ኤ.ቢ.ቢ.አይ. ቫካንሲ እና ኤ.ቢ.ቢ.አይ. ጨረታ) በማሣተም ሥራ የጀመረው ድርጅቱ፣ ጋዜጦቹን ተራ በተራ በማጠፍ በኤ.ቢ.ቢ.አይ. ዊክሊ ስር ጠቅልሎ እያሳትም የነበረ ሲሆን፣ ካለፈው ሣምንት ጀምሮ ለሠራተኞቹ የአንድ ወር የሥራ ማፈላለጊያ ጊዜ በመስጠት ጋዜጠኞቹን መበተኑ ታውቋል።
ከዚህ በፊት ዶ/ር ፍስኃ እሸቱ በፕሬዝዳንትነት በሚመሩት ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ስር “ዕለታዊ አዲስ” የተባለ ጋዜጣ ሲያሣትሙ ቆይተው መበተናቸው የሚታወስ ሲሆን፤ “ኤ.ቢ.ቢ.አይ. ዊክሊ” ለሁለተኛ ጊዜ አቋቁመው የበተኑት ጋዜጣ ነው። በተጨማሪም ዶክተሩ ከተሠጣቸው ፍቃድ ወጪ ማይ ፋሽን የተባለ መጽሔት በማሣተምና በማሠራጨት ተከስሰው ፍ/ቤት ቀርበው ነበር።
በእንግሊዘኛ ቋንቋ ይታተም የነበረው ማይ ፋሽን መጽሔት ፋሽን ከተባለ በአማርኛ ቋንቋ ከሚታተም መጽሔት ጋር በስም በመመሳሰሉ ምክንያት ስያሜውን እንዲቀይር በማስታወቂያ ሚኒስቴር ቢነገራቸው ስያሜውን ለመቀየር ባለመፈለጋቸው የፕሬስ ሥራ ንግድ ፈቃዳቸው እንዲታገድ ቢደረግም፣ ድርጅቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የዕግድ ትዕዛዝ በመተላለፍ መጽሔቱን አሣትሞ በማሠራጨቱ ፍ/ቤት ለመቅረብ ተገደው ነበር።
ፍ/ቤቱ በታገደ የፕሬስ ፍቃድ ሕትመቶችን በማተምና በማሠራጨት በድርጅቱ ሥር የሚሠሩትን 13 ሠራተኞችም በግብረ አበርነት አብሮ ከሷል።
ኤ.ቢ.ቢ.አይ. ዊክሊ ጋዜጣ በአማርኛ የሚታተም ባለሙሉ ቀለም እና 24 ገጽ ጋዜጣ የነበረ ሲሆን፤ የተሰናበቱት ጋዜጠኞች ወደ አስር እንደሚጠጉ ለማወቅ ችለናል።
ዶ/ር ፍስኃ በዩኒቲ ኮሌጅ ስር ያሳትሙት የነበረውና በ1993 ዓ.ም. የህወሓትን መሰነጣጠቅ ተከትሎ ሕትመቱ እንዲቆም ያደረጉት “ዕለታዊ አዲስ” ጋዜጣ፤ በወቅቱ 120 ጋዜጠኞች ተቀጥረው ይሠሩበት የነበረ ሲሆን፤ ሁሉንም ጋዜጠኞች በወቅቱ መበተናቸው አይዘነጋም። ዶ/ር ፍስኃ በወቅቱ ለጋዜጠኞቹ የህወሓትን መሰንጠቅ እንዳይዘግቡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋቸው የነበረ ሲሆን፣ አዘጋጆቹና ጋዜጠኞቹ ከቅጥር በፊት ዶክተሩ በሥራቸውና በጋዜጠኝነት ሙያቸው ውስጥ ጣልቃ እንደማይገቡ የገቡትን ቃል መግባታቸውን አስታውሰው የህወሓትን መሰንጠቅ በመዘገባቸው ጋዜጣውን ዘግተው፤ ጋዜጠኞቹን ማባረራቸው ይታወሳል።