የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ደህንነት አደጋ ላይ ነው
በቀን አራት መኪኖች ይከታተሏቸዋል
Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. December 26, 2008)፦ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ደህንነት አደጋ ላይ መሆኑንና በየቀኑ አራት መኪኖች እንደሚከታተሏቸው የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አረጋገጡ።
ሊቀመንበሯ በሚንቀሳቀሱበት ቦታ ሁሉ በተለይ ስማቸው በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መነሳት ከጀመረ አንስቶ አራት የደህንነት መኪኖች ሲከታተሏቸው እንደሚውሉና በዛሬው ዕለት ደግሞ ሦስት መኪኖች ቤታቸው መግቢያ አካባቢ ድረስ መታየታቸውን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
ወ/ት ብርቱካን ከታሪካዊው ምርጫ 97 ዓ.ም. በኋላ ለሁለት ዓመት የእስር ጊዜ በኋላ ከእስር የተፈቱበትን ምክንያት በሽምግልናው ጥረት ነው በማለት አውሮፓ ለሚገኙ ነዋሪዎችና የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎች ንግግር አድርገዋል በሚል ሰሞኑን በፌደራል ፖሊሶች በተደጋጋሚ ለምርመራ የቀረቡ ከመሆኑም በላይ አገዛዙ በሚቆጣጠራቸው የመገናኛ አውታሮች ከፍተኛ የማስፈራራት ዘመቻ ሲካሄድባቸው መሰንበቱ ይታወቃል።
ወ/ት ብርቱካን ጉዳዩን በሚመለከት ሀገር ቤት በሚታተሙ ጋዜጦች ዛሬ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በንግግራቸው ያነሱበትን ምክንያት የሚዘረዝር እንጂ ይቅርታ ያዘለ አለመሆኑን ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።
የአንድነት ፓርቲ አካሄድ አገዛዙን ክፉኛ ስጋት ውስጥ ከቶታል የሚሉት የሁልጊዜ ተባባሪያችን የሆኑ የፖለቲካ ተንታኝ፤ ፓርቲው በጣም በእርጋታ የሚያደርገው የፖለቲካ እንቅስቃሴና በህዝብ ዘንድ ዘልቆ ለመግባት የሚያደርገው ጥረት ደረጃውን የጠበቀ ከመሆኑም በላይ በህዝብ ዘንድ እያሳደረ ያለው ታማኝነት ኢህአዴግን የሚያስቆጣ ነው ብለዋል።
እኚሁ ተንታኝ እንደሚሉት የአንድነት ፓርቲ እንቅስቃሴ የስሙን ፈቃድ ከማግኘት ጀምሮ እስከ በየክፍለ ሀገራቶች ጽሕፈት ቤቶችን መክፈት ከዛም አልፎ በውጭ ሀገር የሚገኙ ነዋሪዎችን ለማስተባበር ቀስ በቀስ የሚያደርገውን ጥረቶች ውጤታማነት የአገዛዙን የደህንነት ሰዎች እንዲቅበጠበጡ አድርጓል ብለዋል።
ሽምግልናውና ይቅርታው ተነጣጥለው መታየት አለባቸው የሚሉት ሌላ አስተያየት ሰጪ፤ ደግሞ ወ/ት ብርቱካን የተፈታነው በሽማግሌዎቹ ጥረት ነው ማለታቸው በተጨባጭ እውነታ ያለው ነው፤ የይቅርታ ደብዳቤ አልፈረምንም ስትል በየትኛውም መድረክ ስትናገር አልተሰማም ብለው መንግሥት ነገሮች የተምታቱበት ይመስላል ብለዋል።
በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የተነሳውን አለመግባባት በሚመለከት የጠየቅናቸው የፖለቲካ ተንታኝ በድርጅቱ ውስጥ አለመግባባት መፈጠሩ የድርጅቱን ጤነኛነት የሚያሳይና ክርክሮች መኖራቸው ድርጅቱ ውስጥ የዲሞክራሲ ባህል እየዳበረ መሆኑን አሳያል ካሉ በኋላ፤ ድርጅቱ ችግሮቹን በመፍታት ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባዋል በማለት አስተያየታቸውን ደምድመዋል።