መኢአድ ዋና ፀሐፊውን ከሥራ ማሰናበቱን የጽ/ቤቱ በር ላይ በመለጠፍ አሳወቀ

Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. December 26, 2008)፦ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊና የፓርቲው ልሳን (አንድነት) ጋዜጣ፣ ዋና አዘጋጅ ወይዘሪት መሶበወርቅ ቅጣው ከእስር ተለቀቁ።

 

ማክሰኞ ታህሳስ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. ከጽሕፈት ቤታቸው ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት መወሰዳቸውንና በማግስቱ ረቡዕ ታህሳስ 15 ቀን 2001 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው በ600 ብር ዋስ ከእስር መለቀቃቸውን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል።

 

ወይዘሪት መሶበወርቅ የተከሰሱበት ምክንያት በአንድነት ጋዜጣ ታኅሳስ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. በወጣው ዕትም፣ በስዊድን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት ያደረጉትን ሠላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ ከቀረበው ዘገባ ጋር የናዚ ዓርማ ያለበት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፎቶግራፍ በጋዜጣ በማውጣታቸው መከሰሳቸውን ለማረጋገጥ ችለናል።

 

በተያያዘ ዜና መኢአድ (የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት) ባለፈው ሣምንት የድርጅቱን ዋና ፀሐፊ ማሰናበቱን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ያስረዳል። ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ ዋና ፀሐፊው አቶ ወንደሰን ተሾመ መኢአድ ጽሕፈት ቤት መደበኛ ሥራቸውን ለማከናወን ሲያመሩ በሩ ላይ ከፓርቲው መሰናበታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ተጽፎ እንደጠበቃቸው ለመረዳት ተችሏል።

 

የአሁኑ የመኢአድ ከፍተኛ አመራሮች የቅንጅት አመራሮች ከእስር ከተፈቱና በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በተለያዩ ዓለማት ተዘዋውረው ወደ ሀገር ቤት እንደተመለሱ፤ የአሁኑን የአንድነት አመራሮች ከመኢአድ ጽሕፈት ቤት በተመሳሳይ መልኩ በር ላይ እንዳይገቡና ከድርጅቱ መሰናበታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፈውላቸው እንደነበር አይዘነጋም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!