Ethiopia Zare (ዓርብ መጋቢት 18 ቀን 2001 ዓ.ም. March 27, 2009)፦ በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል የሚመራው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ (መድረክን) ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረቡን የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ምንጮች ገለጹ።

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች እንደገለጹት፤ አንድነት ፓርቲ ከመድረክ ጋር በጋራ ለመሥራት መስማማቱን ይፋ ካደረገ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ወደ አስር የሚጠጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ በቅርቡ ጥያቄውን ያቀረበው መኢአድ መሆኑ ታውቋል።

 

መኢአድ ለመድረኩ በጻፈው ደብዳቤ፤ መድረኩን ለመቀላቀል ፍላጎት ያለው መሆኑን በመግለጽ ይህን ለማድረግ እንዲያስችለው መድረኩ አለኝ የሚለውን ሰነዶች እንዲልክለትና እንዲያየው ጠይቋል።

 

በቀድሞው መከላከያ ሚንስትር አቶ ስየ አብርሃ፣ በቀድሞው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና በአራት የፖለቲካ ድርጅቶች የተመሰረተውን መድረክ ለመቀላቀል ጥያቄ በማቅረብ ላይ ያሉትና አስቀድሞ ተቀላቅለው የሚገኙት የፖለቲካ ድርጅቶችና ድርጅቶቹን የሚመሯቸው ግለሰቦች ላለፉት በርካታ ዓመታት በጋራ መሥራት አቅቷቸው ሲጣሉና የመሰረቷቸውን ፓርቲዎች ሲያፈርሱ የነበሩ፣ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ፖለቲከኞች የሚገኙበት ሲሆን፤ መኢአድ ለመቀላቀል ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ካገኘ፤ ለመድረኩ በቅርብ ጊዜ መፍረስ አመላካች መሆኑን ከወዲሁ የሚተነብዩ አልታጡም።

 

የዓረና ሊቀመንበርና የመድረኩ ሰብሳቢ አቶ ገብሩ አስራት ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው፤”መድረኩን ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ ፓርቲዎችን ማመልከቻዎች እየተመለከትናቸው ነው፤ ቀደም ሲል የተጣሉ ካሉ ደግሞ እናስታርቃቸዋለን” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!