ክሱ በሕገወጥ የመኪና ዝውውር በሚል ነው

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ታህሳስ 18 ቀን 2001 ዓ.ም. December 27, 2008)፦ የኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ የንግድ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ጽ/ቤት ዘጠኝ የሥራ ኃላፊዎች፣ ቀረጥና ታክስ ያልተከፈለባቸውን ከ15 በላይ ተሽከርካሪዎች፣ በሕገወጥ መንገድ የተሠሩ ሐሰተኛ የባለቤትነት ደብተር፣ ሠሌዳ ቁጥሮችንና የማዘዋወሪያ ቅፆች መሆናቸውን እያወቁ ተለዋጭ ካርታና ሊብሬ ሰጥተዋል ሲል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ክስ መስርቶባቸዋል። በድርጊቱ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊና ተባባሪ ናቸው ባላቸው 29 ተጠርጣሪዎች ላይም ተመሳሳይ ክስ አቅርቧል።

 

ፀረ ሙስና ኮሚሸን ባለፈው ሣምንት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው የክስ ማመልከቻ፣ ዘጠኙ የሥራ ኃላፊዎች 14 ለሚሆኑት አብረው ለተከሰሱ የቀረጥና ታክስ ተጠቃሚዎች በ1998 እና በ1999 ዓ.ም.፣ ከቀረጥ ነፃ የገቡ 14 ተሽከርካሪዎችን ቀረጥና ታክስ ሳይከፈልባቸው አብረዋቸው ለተከሰሱና ለሌሎች ግለሰቦች በሕገ ወጥ መንገድ አዘዋውረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

 

ተከሳሶቹ ከቀረጥ ነፃ የገቡና እንዴት እንደገቡ ያልታወቁ ተሽከርካሪዎችን፤ ሐሰተኛ የሆነ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የማዛወሪያ ቅጽ አዘጋጅተው ኦሮሚያ ክልል በመሄድ፣ ተለዋጭ ሰሌዳ በመውሰድ መኪኖቹን መሸጣቸውን ፀረ ሙስና በክሱ የገለፀ ሲሆን፤ በሕጋዊ መንገድ ቀረጥና ታክስ ቢከፈል ኖሮ መንግሥት ማግኘት የነበረበትን 1 ሚሊዮን 755 ሺህ 585 ብር አጥቷል ብሏል።

 

ተከሳሾቹ ኮዳቸው አዲስ አበባ የሆኑ ተሽከርካሪዎች በተለያዩ ምክንያት ጠፍተው በምትክ የተሰጠባቸውን የሠሌዳ ቁጥሮችን፣ የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት መ/ቤት ማሕተሞችን፣ የሥራ ኃላፊዎች ፊርማዎች፣ የሥምና የሥራ ማዕረግ ቲተሮች ያለአግባብ በመጠቀም፣ ሐሰተኛ የሆኑ መንግሥታዊ የባለቤትነት ደብተሮችን፣ የማዘዋወሪያ ቅፆችን እና የተሽከርካሪ መለያ ሠሌዳ ቁጥሮችን በየስማቸውም ሆነ በሌላ ሰው ስም በሐሰት አዘጋጅተው፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ አዳማ (ናዝሬት) እና ቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ንግድ ትራንስፖርትና ቱሪዝም ጽ/ቤት አቅርበው፣ የሥራ ኃላፊዎቹም የቀረቡት የማዘዋወሪያ ቅፆችም ሆኑ ሊብሬዎች ሐሰተኛ መሆናቸውን እያወቁ፣ ተለዋጭ ሰሌዳ ቁጥሮችንና ሊብሬዎችን በመስጠታቸው በአጠቃላይ በ38 ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቷል።

 

ዓቃቤ ሕግ ክሱን ለፍርድ ቤቱ ካቀረበ በኋላ፣ 38ቱን ተከሻሾች አፈላልጎ ለማግኘት ግዜ የሚያስፈልገው መሆኑን በመግለጽ፣ ረዘም ያለ ቀጠሮ በመጠየቁ 38ቱ ተከሳሾች እንዲቀርቡ ለአንድ ወር ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ