W/t Birtukan Mideksaወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሽምግልናውን ጉዳይ አስመልክቶ የሰጡት ቃል

ታህሳስ 14 ቀን 2001 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ጽ/ቤት ተገኝቼ ማስጠንቀቂያ ሲነገረኝ እና ያው መልዕክት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሲተላለፍ ስመለከት ያደረብኝን ስሜት ለመግለጽ ያዳግተኛል።

 

ምንም እንኳን ይህን ሁኔታ ለመለወጥ፣ ከማውቀውና ከማምነው ነገር ውጭ የምናገረው ነገር ባይኖርም ጉዳዩ በህዝብ ዘንድ ጥያቄዎችን ማጫሩ አልቅረምና በጉዳዩ ላይ ግንዛቤን ለመፍጠር ይቺን ጽሑፍ ለመጻፍ ወስኛለሁ። ምናልባትም የመጨረሻ ቃሌ ይሆናል።

 

በሽምግልናው ልጀመር። የሽምግልናው መሰረታዊ መንፈስ፣ ሁለቱንም የሚያግባባ ስምምነት አምጥቶ እና የዕርቅን መንፈስ ፈጥሮ የፖለቲካ ሂደቱን ማስቀጠል ነበር። ይህም በመሆኑ ነው ሂደቱ በርካታ ወራትን ሊወስድ የቻለው። በዚህም ውስጥ ምርጫ 1997 ዓ.ም. ተከትሎ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ፣ የሀገር ሽማግሌዎች “አንዱን አጥፊ አንዱን ንጹኅ በማድረግ ሳይሆን እያንዳንዱ ወገን በወቅቱ ለተፈጠረው ችግር ህዝቡን ይቅርታ ጠይቆና እርስ በርሱም ተጠያይቆ በመሰረታዊ ጉዳዮችም ያለውን የፖለቲካዊ አመለካከት ቁርጠኝነትን አረጋግጦ፣ በዕርቅ መንፈስ ወደፊት በጋራ ለመቀጠል” በሚል ዓላማ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች፣ ለሁለቱም ወገኖች ሲያቀርቡ ሃሳባችንን ሲያለዋውጡና በተቻለም መጠን ለማለዘብም ሲሞክሩ ቆይተዋል።

 

ከዚህም የተነሳ በመንግሥት ፈቃደኝነት ብቻ ሳይሆን በእኛም ተሳትፎም ጭምር፣ በሀገር ሽማግሌዎች ሲደረግ የነበረው ሽምግልና ሁለቱም ወገኖች ሰጥተውና ተቀብለው የሚያመጡት ማስማሚያ ሃሳብ /Negotiated Deal/ በመድረስ ላይ ያተኮረ ነበር።

 

በሂደቱ መንግሥትም ለሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ያለውን ታማኝነት እንደገና እንደሚያረጋገጥ፣ እና ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ችግር ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን እና ቤተሰቦችን ለመካስ ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም፤ ውይይቱ እየቀጠለ ሲሄድና የፍርድ ቤቱ ክርክር ወደ ብይን በሚቃረብበት ወቅት በሽማግሌዎች አስተባባሪ አማካይነት አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ተነገረን።

 

ይኸውም ሌላኛው ወገን፣ እኛ ታሳሪዎች ከህዝብ እና ከመንግሥት ይቅርታ ከምንጠይቅበት ነጥብ ውጭ በተለይም መንግሥትን የሚመለከቱ የወጡት ነጥቦች ላይ መስማማት አይፈልግም የሚል ነበር። ይሁን እንጂ በዚህም ደረጃ የውይይቱ አቅጣጫ የተመሰረተበት የዕርቅ መንፈስ አልተቀየረም ነበር። ስለሆነም ሽማግሌዎቹ ሌሎች የመግባቢያ ሃሳቦችን ወደኋላ የተተወ ቢሆንም በሀገራችን ባህል ይቅር በመባባል መንፈስ የተቃኘውን ያንን ሰነድ ብንፈርም ጉዳዩ ባለበት ደረጃ እንደሚቆም ፋይሉም እንደሚዘጋ ገልጠው ሽምግልናውን ገፉበት። ቃል በቃል በመግልጽም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይህ ሰነድ ከተፈረመ የሥራ አስፈጻሚ ሥልጣኔን ተጠቅሜ ክሱ እንዲቋረጥ አደርጋለሁ” እንዳሉ አረጋገጡልን።

 

ከዚህ ጋር በተያያዘም “በሀገሪቷ ውስጥ ከቅንጅት ጉዳይ ጋር በተያያዘ የታሰሩ እስረኞች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚፈቱ በመንግሥት እና በቀድሞው ቅንጅት መሪዎች መሃከልም የፖለቲካ ውይይት በቀጥታ እንደሚጀመር የፓርቲው መሪዎች ያለምንም ገደብ የፓርቲውን ሥራ እንደሚቀጥሉ” ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።

 

በተጨማሪም ይህ ሰነድ በማንኛውም መንገድ ለምንም አይነት የፕሮፖጋንዳ ጥቅም በሁለቱም ወገኖች እንደማይውልና ሰነዱም የሚፈረመው ለሽማግሌዎች እንደሆነ፣ ሽማግሌዎችም በዚያ ላይ ተመስርተው የራሳቸውን ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚጽፉ በሽማግሌዎች የተረጋገጠ መሆኑ ታሳቢ ሆኖ ሰነዱ ተፈረሟል።

 

በርግጥም በዚህ ሰነድ ላይ እኔም እንደ አንድ ታሳሪ መፈረሜን ክጄ አላውቅም። በሽማግሌቹም የዕርቅ መግባቢያ መንፈስ መሰረት፣ በፖለቲካ የተቀሰቀሰውን ክስ ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት በማሰብ ለዕርቅ ስል ከሌሎች የፓርቲው መሪዎች ጋር ተስማምቼ ሰኔ 11 ቀን 1999 ዓ.ም. በተጻፈው ሰነድ በሽማግሌዎች አማካኝነት መንግሥትንና ህዝብን ይቅርታ ጠይቄአለሁ። ይህ ብፈልግም ልለውጠው የማልችለው ሐቅ ነው።

 

ከዚህ ስምምነት በኋላ ይጠበቅ የነበረው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሽማግሌዎቹ አረጋግጠው በሰጡት ቃል መሰረት የክሱ መቋረጠና የፋይሎ መዘጋት ቢሆንም ሂደቱ ሌላ አዲስ መልክ ያዘ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የዓቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ክሱን ሳያቋርጥ ቀረ። ይልቁንም ተከሳሳቹ ዕድሜ ልክ ቅጣታችንን ተቀበልን። ከዚህ በኋላ እንግዲህ ታሪኩ በእኛ ስምምነት ሳይሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈቃድ የተቃኘ ነው። ጉዳዩም ብሎ ብሎ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ለታሳሪዎች በሰጡት ይቅርታ እኛ ከእስር በመፈታታችን ተገባደደ።

 

እንግዲህ እንዲህ ያለ የተዥጎረጎረ መልክ ያለውን ውስብስብ ሂደት በመደበኛው የሕግ የይቅርታ አቀራረብ ስነሥርዓት እንደቀረበም በዛውም አግባብ እንደተደመደመ ጉዳይ ብቻ ለማየት መሞከር አንድም እራስን ማሞኘት ነው፤ ሌላም አለማወቅ።

 

አንድ ተከሳሽ በሕጉ መሰረት የይቅርታ ጥያቄ ማቅረብ ያለበት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይሆን ለይቅርታ ቦርድ ነው። በኛ ጉዳይ ለሀገር ሽማግሌዎች የፈረምነውን ሰነድ ለይቅርታው ቦርድ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው። ይቅርታውንም የጠየቁት እርሳቸው ናቸው ብሎም መከራከር ይቻላል። ሆኖም ግን በሕጉ አግባብ የይቅርታ ጥያቄ ማቅረብ የሚችለው ባለጉዳዩ፣ ጠበቃው ወይም ቤተዘመድ እንጂ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አይደለም።

 

ጥያቄው መቅረብ የሚችለውም በጉዳዩ ፍርድ ቤት ፍርዱን እና ቅጣቱን አጠናቅቆ ከወሰነ በኋላ እንደሆነ በሕጉ ተመላክቷል። በእኛ ጉዳይ ከመነሻው ጉዳዩን የየቅርታ /Pardon/ የመጨረስ ስምምነት ስላልነበረን ለሽማግሌዎች የተፈረመው ሰነድ የተፈረመው ፍርድ ቤት በጉዳዩ የቅጣት ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ነው።

 

ስለዚህ ከዚህ እውነታ በመነሳት በዚሁ በሕግ በተሰመረ አግባብ የይቀርታ ጥያቄ አላቀረብኩም። ሆኖም ግን በመጨረሻ በፕሬዝዳንቱ ለተሰጠው ይቅርታ ጥያቄ መሰረት የሆነውን የሀገር ሽማግሌዎች ለዕርቅ ሲሉ አግባብተው ሰኔ 15 ቀን 1999 ዓ.ም. ያስፈረሙንን ሰነድ ከነይዘቱ አልካድኩም ብሎ መናገሩ የቱ ላይ ነው ስህተቱ? የቱ ላይ ነው ወንጀሉ?

 

በውጭ ሀገር በጉዳዩ የተናገርኩትም ይህንኑ የሚገልጽ እና የሚያብራራ እንጂ ሌላ ምንም የተለየ ይዘት አልነበረውም። ምናልባት የተናገርኩት አላግባብ ተተረጉሞ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ።

 

ይህ የእኔ አንጋገር የተዛባ ነው ቢባልስ ፖሊስ ጣቢያ በመጥሪያም ያለመጥሪያም ለመመላለስ ያበቃል? በፍፁም ያስጠይቃል ቢባልስ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የተሰጠን ይቅርታ የሚያስነሳው እንዴት ይሆን? ይቅርታን የሚያስነሳ ቢሆን ፌደራል ፖሊስ በየትኛው ሕጋዊ ሥልጣኑ ነው በጉዳዩ ምርመራ የሚያደርገው? ማስጠንቀቂያስ የሚሰጠው?

 

ታህሳስ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የወረዳ 12 ፖሊሲ አባላት የሆኑ ሁለት ፖሊሶችን ቤቴ በመላክ ቢሯቸው ድረስ እንድመጣ ሲጠሩኝ ስለ ፓርቲያችን ስለአንድነት ለመወያየት ሊሆን ይችላል በሚል በጽ/ቤታቸው ተገኝኔ የተጠራሁት ከይቅርታው ጋር በተያያዘ መሆኑ ሲነገረኝ መጀመሪያ የጠይኩት ጥያቄ “ፖሊስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሥልጣን አለው?” የሚል ነበር። ምላሾቹ ግን በመነደቅ ፈገግታ የታጀበ “ይሄ እኮ የአካዳሚ ውይይት አይደለም፤ እንዲሁ አይነቱ ጥያቄ ብትተይ ይሻላል” የሚል ነበር። ለእነርሱ ያስፈገጋቸው፣ ያስገረማቸው ጉዳይ ግን እኔን ሁሌም የምኖርለት፣ የምቆምለት፣ እንዳንዴም የምታሰርበት እና የምፈታለት ታላቅ ቁም ነገር ነው። የሕግ የበላይነት ወይም ሕገመንግሥታዊነት።

 

ሕገወጥነትን፣ ማናለብኝነትን መቼም አልለምደውም፤ አልተባበረውም። ስለዚህ ነው ታህሳስ 15 ቀን 2001 ዓ.ም. ፖሊስ ኮሚሽነሩ በድጋሚ ያለ ሕጋዊ መጥሪያ በመልዕክተኛ ወደ ቢሯቸው ሲጠሩኝ በወቅቱ ሳልሄድ የቀረሁት። በዕለቱ ከሰዓት በኋላ የሕግ መጥሪያ በደረሰኝ ጊዜ ወደ ቢሯቸው ለመሄድ ደቂቃም አላጠፋሁም። በኮሚሽነሩ ቢሮ ስደርስ የጠበቀኝና መጥሪያው የሚገልፀው ለየቅል ቢሆንም።

 

ኮሚሽነሩ በላኩልኝ መጥሪያ ላይ እንደተጠቀሰው ጥያቄ ሳይሆን ያቀረቡልኝ መመሪያ ነክ ማስፈራሪያ ነበር። ስዊድን የሰጠሽውን ቃል በሦስት ቀን ውስጥ ካላስተባበልሽ መንግሥት ይቅርታውን አንስቶ እስር ቤት ይከተልሻል የሚል።

 

“ይቅርታውን ማንሳት የሚችሉት እኮ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር እንጂ እርስዎ መንግሥት የሚሉት የሥራ አስፈጻሚ አካል አይደለም። ለዛውም እርሱም ቢሆን ሥርዓት አለው። የ”ይቀርታ ይነሳ” አቤቱታ ቀርቦ፣ በ20 ቀናት ውስጥ ለባለጉዳዩ ደርሶ፣ ቦርዱ ካመነበት ጥያቄው ለፕሬዝዳንቱ ቀርቦ፣ ያኔ ይቀርታው ሊነሳ ይችላል …” እያልኩ ለኮሚሽነሩ ላስረዳቸው አስቤ ነበር፤ አላደረኩትም። ንግግራቸውን መጨረሳቸውን አረጋግጬ ያለ ምንም ቃል ቢሯቸውን ጥዬ ወጣሁኝ።

 

በእኔ እምነት ይሄ ሁሉ ከሕግ የወጣ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰብን ያለው ስለ ቃላት ጨዋታ ወይም ስለ ተዛባ እውነት ወይም ስለተጣሰ ሕግ አይመስለኝም። መልዕክቱ ግልጽ ነው። ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሠላማዊ ታጋዮች። “በሠላማዊና ሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ የፖለቲካ ትግል ማድረግ የሚቻለው በሕገ መንግሥቱ በተሰመረው መስመር ሳይሆን፤ ገዢው አካል ወይም ግለሰቦች በፈቀዱት ብቻ ነው“ የሚል ነው። ለዚህም ደግሞ እሺ ወይንም “አዎ” ማለት ለእኔ እጅግ ከባድ ነው።

 

ብርቱካን ሚደቅሣ

 

ታህሳስ 18 ቀን 2001 ዓ.ም. / December 27, 2008

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ