በስዊድን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በወ/ት ብርቱካን እና በቴዲ አፍሮ እስራት ቁጣቸውን ገለጹ
Ethiopia Zare (ሰኞ ታህሳስ 27 ቀን 2001 ዓ.ም. January 05, 2009)፦ ሰኞ ዕለት በስዊድን ዋና ከተማ በስቶክሆልም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳንና የቴዎድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮ) አለአግባብ መታሰር፤ እየተፈጸመ ያለውንም ግፍና በደል፤ እንዲሁም የዲሞክራሲ መታፈንን፤ በመቃወም በስቶክሆልም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽ/ቤት በራፍ ተገኝተው ቁጣቸውን ገለጹ።
እነዚሁ ቁጥራቸው ወደ ሰላሳ የሚገመት ኢትዮጵያውያን፤ ከጠዋቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ በኤምባሲው ጽ/ቤት በራፍ የተገኙ ሲሆን፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ሆኑትን የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን እና የአርቲስት ቴዲ አፍሮን ፎቶ በመያዝ ሁለቱም የህሊና እስረኞች አለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
እንዲሁም የኢህአዲግ መንግሥት ኢትዮጵያን አይወክልም፤ የግፍ አገዛዝ በቅቶናል፤ ከእንግዲህ ሀገርና ህዝብ አጥፊዎች ላይ በጋራ እንነሳለን፤ ... የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን አሰምተዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተቆለሉ የመከራ የድህነትና የሰቆቃ አምራች ኃይሎችን ተሸክመን አንኖርም ሲሉም ተደምጠዋል።
በቦታው ላይ መፈክሮች ከማሰማት ውጪ ምንም አይነት ረብሻና ኹካታ ባይፈጠርም፤ የስዊድን የፖሊስ አባላት ሲያንዣብቡ ቆይተዋል። ሆኖም ከኤምባሲው ሠራተኞች መካከል ግን አንዳቸውም ሲገቡና ሲወጡ እንዳልታዩ በኤምባሲው መግቢያ ላይ የተገኙ የዓይን ምስክሮች ገልጸዋል።
የኤምባሲው ሠራተኞች በአካባቢው አለመገኘትን አስመልክቶ ስለጉዳዩ የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ያነጋገራቸው አንድ አስተያየት ሰጪ፤ ”ሀገሪቷንና ህዝቡን በኃይል አምቆ ዲሞክራሲን፣ ፍትህንና ነፃነትን አሳጥቶና ነስቶ የሚገኘው የኢህአዲግ መንግሥት የሚያደርሰው ግፍና በደል የራሱን የኢህአዲግ ደጋፊዎቹን በማሳፈርና በማሸማቀቅ ላይ እንደሚገኝ ምስክር ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።



