አለም አቀፍ ተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ
Ethiopia Zare (ሰኞ የካቲት 23 ቀን 2001 ዓ.ም. march 2, 2009)፦ በቅርቡ ወደ እስር የተጣለችውን አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበርን ጨምሮ ያለፍትህ በእስር ቤት የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ዘንድ የሚጠይቀው በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያኖች ዛሬ ሰኞ በተለያዩ ሀገራት ዋና ዋና ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ እያካሄዱ ነው።
በተለይ በአሜሪካ ርእሰ ከተማ በዋሽንግተን ዲሲ ብዛት ያላቸው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ‘መለስ ዜናዊ ገዳይ ነው’ ‘አሜሪካ በኢትዮጵያ ፍትህ እንዲሰፍን ታግዝ’ ፣ ‘አሜሪካ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ትተባበር’ ፣ ‘ፕሬዝዳንት ኦባማ ለአምባገነን እርዳታ ያቁሙ’ የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን በማሰማትና በአለማቀፉ ሰልፍ አስተባባሪዎች ተዘጋጀውን ደብዳቤ ለሚመለከተው ክፍል በማድረስ ላይ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን በሌሎች የአውሮፓ ሀገራት በለንደን በጀርመን በሲዊድንና በሌሎች ከተሞችም ተመሳሳይ ሰልፎች መደረጋቸው ታውቋል።
በቫንኩቨር-ካናዳ ተመሳሳይ ሰልፍ ከእኩለ ቀን ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን ሰሞኑን በቫንኩቨር ነዋሪ ሴቶች ለከተማው ባለስልጣናትና ለፓርላማ ተመራጮች በእስር ላይ የምትገኘውን ብቸኛ የሴት ፖለቲካ ድርጅት መሪ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ሁኔታ ሲያስረዱና የካናዳ መንግስት ለኢትዮጵያ አገዛዝ የሚያደርገውን እርዳታ እንዲያቆም ሲያደርጉ ከመሰንበታቸውም በተጨማሪ በዛሬው እለት የአካባቢው ነዋሪዎች ቫንኩቨር በሚገኘው የአሜሪካ ካውንስለር ጽ/ቤት በመገኘት ተዘጋጀውን ደብዳቤ ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባም መንግስት የሚልኩ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።



