ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳና ቴዲ አፍሮ በጉልህ ይጠቀሳሉ

በሲያትል ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነው

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ታህሳስ 28 ቀን 2001 ዓ.ም. January 06, 2009)፦ ያለአግብብ የታሰሩ እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ታላቅ ዓለማቀፍ ሠላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግና በተለይ እውቁን ድምጻዊ ቴዲ አፍሮንና የመጀመሪያዋን የኢትዮጵያ ሴት የፖለቲካ ድርጅት መሪ የሆነችውን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ሁኔታ በጉልህ የሚያሳይ ዓለማቀፍ የአዘጋጅ ኮሚቴ ተቋቋመ።

 

ረቡዕ ጃንዋሪ 14/2009 በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በትውልድ ሀገራቸው የሚካሄደውን የማናለብኝነት የሕግ ጥሰት ለዓለም ማኅበረሰባትና መንግሥታት በአንድነትም ሆነ በተናጠል እንዲያሳውቁ ይሄው አዘጋጅ ኮሚቴ የገለጸ ሲሆን፣ በተለይ ብዙ ኢትዮጵያዊያኖች በሚኖሩባቸው ከተሞች በሕብረት በመውጣት የአገዛዙን የሕግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማሳየት ጉልህ ሚና መጫወት እንደሚኖርባቸው ተጠቁሟል።

 

በሰልፉ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር በእስር የሚንገላቱትንና ፍትህ አጥተው የሚሰቃዩ ወገኖችን ሁኔታና በተለይ በአሁኑ ሰዓት በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በእጅጉ ያስቆጣውን የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑትን የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን እና ዝነኛውን የሙዚቃ ባለሙያ ቴዎድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) ሁኔታ በጉልህ በማሳየት (ኃይላይት በማድረግ) የተቃውሞው ሰልፍ እየተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

 

ይህንኑ የሠላማዊ ሰልፍ በመደገፍና በመተባበር ጃንዋሪ 14/09 በሲያትል አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ከፍተኛ ዝግጅት እያካሄዱ መሆኑን አዘጋጆቹ ጠቁመው፤ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የዚህን አስከፊ አገዛዝ ለማጋለጥ በሲያትል ሲቲ ሴንተር ሰልፍ የሚደረግ ከመሆኑም በላይ ለከፍተኛ የመንግሥት አካላት በተለይም በኮንግረስና ሴኔት አካባቢ ትኩረት እንደሚደረግ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

 

በሲያትል የሚካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ አጎራባች የሆኑት የቫንኩቨርና የፖርትላንድ ነዋሪዎችም እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ