ሁለቱ አንጋፋ ተቃዋሚዎች እንደተለመደው ወንበሩን ተቀያየሩት

Ethiopia Zare (ኀሙስ ሚያዝያ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. April 9, 2009)፦ ተቃውሞአቸውን ባሰሙ ቁጥር የአቶ መለስን ሥልጣን የሙጥኝ ማለት ደጋግመው የሚያስታውሱን ሁለቱ አንጋፋ ተቃዋሚዎች የፓርቲያቸውን ወንበር ለዓመታት እየተቀያየሩ ያለተተኪ መቀጠላቸውን አላቋራጡም። የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት (ኢዴኃኅ) ባካሄደው አራተኛ መደበኛ ጉባዔ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ሊቀመንበር ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።
ፓርቲው ከትንናት በስቲያ ማክሰኞ ዕለት በመግለጫው እንዳስታወቀው መጋቢት 19 ቀን 2001 ዓ.ም. ባደረገው ጉባዔ፤ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን በሚደረገው ትግል ከተቃዋሚው ጎራ በመሰለፍ ቀዳሚውን ስፍራ የያዙትን ዶ/ር መረራ ጉዲና በሊቀመንበርነት ማስመረጡንና ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስ የም/ሊቀመንበርነት ቦታ መያዛቸው አስታውቋል።
አስተያየት ሰጪዎች ይህን አስመልክተው እንደሚናገሩት፤ ሁለቱ ሰዎች በተቃውሞ ፖለቲካው ጎራ ውስጥ ያለተተኪ እና ያለለውጥ የአቶ መለስን የሥልጣን ዕድሜ ያህል የቆጠሩ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ አሁንም ይህ ሁኔታ መቀጠሉ እነሱ በሚያደርጉት ትግል ትንሽም ቢሆን ለውጥ እንዳይታሰብ ያደርጋል የሚል ነው።
አንድ ፓርቲ ለበርካታ ዓመታት በሚያደርገው ትግል አምባገነን መንግሥትን በአጭር ጊዜ መቀየር ባይቻል እንኳን በርካታ ደጋፊዎችና ተተኪ አመራሮች በማፍራት ፓርቲውን ማጠናከር እንደሚቻል ጠቁመው፤ ሁለቱ ተቃዋሚች ግን ምርጫ በመጣ ቁጥር ወደ ትውልድ አካባቢያቸው በመሄድ ያችኑ የፓርላማ ወንበራቸውን ካስጠበቁ በኋላ ምን ያህል አባላት እንዳላቸው በቁጥር እንኳን የማይታወቀውን የፓርቲያቸውን ሥልጣን የፊጥኝ በማለት የአቶ መለስ አቻ ከመሆን ያለፈ ተግባር አልሠሩም ብለውናል እነኚህ አስተያየት ሰጪዎች።
እንደውም እነኚህ ተቃዋሚዎች ኢህአዲግ፤ “መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን አስፍቶ ተቃዋሚዎች በሚገባ እየተንቀሳቀሱ ነው፣ ፍትሃዊ ምርጫም እየተካሄደ ፓርላማ ገብተው ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ነው” በሚል ለዓለም መንግሥታት ለሚሰጠው መግለጫ ጥሩ ሽፋን ሆነውለታል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች የራሳቸውን ሃሳብ ይሰነዝራሉ።



