አዲስ አበባ ራጉዔል ቤ/ክ አካባቢ ቦንብ ፈነዳ
በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል
Ethiopia Zare (ዓርብ የካቲት 21 ቀን 2000 ዓ.ም. / February 29,2008)፦ ዛሬ ረፋዱ ላይ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ መርካቶ በሚገኘው ራጉዔል ቤተክርስቲያን አካባቢ "ቁጭራ" በሚባለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ አጠገብ ቦንብ ፈንድቶ በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ሰዓት ድረስ በሰው ሕይወት ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለማወቅ አልቻልንም።
ቦንቡ ከፈነዳበት ሰዓት ጀምሮ ከሁለት ሰዓታት በላይ የአካባቢው መንገዶች ተዘግተው የነበረ ሲሆን፣ ከፍተኛ የፀጥታ መታወክ በአካባቢው እንደነበር በስፍራው የተገኘው ሪፖርተራችን ገልጦልናል።
ፍንዳታው በተከሰተበት አቅራቢያ "ዑመር ሰመተር" የተሰኘው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚገኝ ሲሆን፣ ቦንቡ በፈነዳበት ሰዓት በት/ቤቱ ቅጽር ግቢ ተማሪዎች ነበሩ። ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤቱ ሰድደው የነበሩ ወላጆች በአካባቢው ተገኝተው ወደ ት/ቤቱ ለሄድ ቢፈልጉም መንገዶቹን ፖሊስ ከሁለት ሰዓታት በላይ ዘግቷቸው ነበር።
በሁኔታው የተረበሹና ልጆቻቸው የአደጋው ሰለባ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ የጓጉና በሁኔታው የተረበሹ ወላጆች በርካቶች እንደነበሩ ለማወቅ ችለናል።



