Ethiopia Zare (ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 2000 ዓ.ም. March 1,2008)፦ ቅዳሜ ማምሻውን የተሰበሰበው የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ላዕላይ ምክር ቤት ድርጅቱን በአዲስ ስም ለማስመዝገብ የወሰነ ሲሆን፣ በጎደሉ የሥራ አስፈጻሚ ምትክም አምስት አባላትን የመረጠ መሆኑን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ጠቆመ።

በደረሰን ዘገባ መሰረት ላዕላይ ምክር ቤቱ ባደረገው ጠቅላላ ውሳኔ መሰረት ድርጅቱን እንደ ድርጅት ለማስቀጠል ያለው ብቸኛ አማራጭ በአዲስ ስም አስመዝግቦ መቀጠል መሆኑን በማመን ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል።

በዚህም መሠረት በጎደሉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምትክ ዶ/ር ኃይሉ አርአያን፣ አቶ ተመስገን ዘውዴን፣ አቶ መሐመድ አሊን፣ አቶ አስራት ጣሴን እና አቶ ክፍሌ ጥግነህን በመምረጥ የቅንጅቱን አዲስ ስም በሚመለከት ሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ እንዲሰጥበት በመወሰን ያስተላለፈ ሲሆን፤ በስብሰባ ው ላይ 33 የላዕላይ ምክር ቤቱ አባላት ተገኝተዋል።

ጠቅላላ የምክር ቤቱ አባላት ባለፈው ለማሟያ የተመረጡት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምን ጨምሮ ከተመረጡት አስራ ስድስት አባላት በተጨማሪ በአጠቃላይ  ስድሳ ሲሆኑ፣ ሊቀመንበሩ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውልን ጨምሮ 20 የሚሆኑ የምክር ቤቱ አባላት እስከአሁን ከድርጅቱ ጋር መቀጠላቸውንና ያለመቀጠላቸውን ያላሳወቁ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።

የቅንጅቱን ውሳኔ በሚመለከት ያነጋገርናቸው አንድ የፖለተካ ተንታኝ "የኢህአዴግ አገዛዝ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ በህዝቡ ውስጥ ሰርጾ መግባት በእጅጉ እንዳሳሰበውና ሕልውናውን ጥያቄ ውስጥ ለማስገባት በስሙ ላይና በዓርማው ላይ የወሰደው እርምጃ ቅንጅቱ እንደ ቅንጅት እንዳይቀጥል ያለውን ጽኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነው ..." ካሉ በኋላ "... የሥራ አስፈጻሚው አሁን የወሰደው እርምጃ ኃላፊነት የተሞላበትና ፈቃድ አሰጣጡ ላይ የኢህአዴግን ምርጫ ቦርድ ፈተና ውስጥ የሚጥለው ይሆናል። ..." ከማለታቸውም በላይ "... የወደፊቱን የሀገሪቱን የፖለቲካ ሂደትና የህዝቡን ተሳትፎ ሊያፋጥነው ይችላል ..." በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

  

          

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ