"የተገነጠሉ አባላት ፓርቲውን አጠናክረው ቢቀጥሉ የሚጠላ ወገን የለም" ወ/ት ብርቱካን

Ethiopia Zare (ማክሰኞ የካቲት 25 ቀን 2000 ዓ.ም. March 4,2008)፦ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በዛሬው ዕለት ወደ አዋሣ ከተማ ተጉዘው በቅንጅት ስም ተመርጠው ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ከገቡ 23 አባላት ጋር መወያየታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በዛሬው ዕለት ባደረጉት ጉዞ አዋሣ ከተማ በሚገኘው ያማረ ሆቴል ከአባላቱ ጋር ምሣ ከተገባበዙ በኋላ ከሰዓት ሙሉውን ስብሰባ ማድረጋቸውን ታውቋል።

 

በስብሰባው ላይ አባላቱ ለሊቀመንበሯ በርካታ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከጥያቄዎቹ መካከልም "ቅንጅቱ በምን መንገድ መቀጠል ይችላል?" የሚል ነበር።

 

ሊቀመንበሯም ለጥያቄዎቹ በተሳካ ሁኔታ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ቅንጅት ስሙን ቀይሮ በአዲስ ስም በመመዝገብ እንዲቀጥል መወሰኑንና ይህንንም ሥራ አስፈጻሚው እንዲያስፈጽም መባሉን ገልጸውላቸዋል።

 

ቅንጅት ስሙን ይቀይር እንጂ ዓላማው የማይሞትና የሚቀጥል መሆኑን ወ/ት ብርቱካን ገልጸው፣ በቅርብ ጊዜም የፓርቲው ሕጋዊነት ተረጋግጦ ሁሉም የተዘጉ ቢሮዎች እንደሚከፈቱ ቃል ገብተውላቸዋል።

 

ከፓርቲው ራሳቸውን ያገለሉም ሆነ በተለያየ ምክንያት የተገነጠሉ አባላት ተቀላቅለው ፖርቲውን አጠናክረው ቢቀጥሉ የሚጠላ ወገን እንደሌለ ገልጸው፤ ድርጅቱ ለተነሳለት ዓላማ የሚቆም ማንኛውም አባል ፓርቲውን መቀላቀል ይችላል ብለዋል። ለፓርቲው ሁሉም ጠንክሮ መሥራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

 

በነገው ዕለትም በደቡብ ክልል አንድ ሌላ ከተማ ተጨማሪ ጉዞ እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገልጸዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ