የጉጂ እና የቦረና ጎሣዎች ተጋጩ
በግጭቱ ደን ተቃጠለ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ የካቲት 25 ቀን 2000 ዓ.ም. March 4,2008)፦ በጉጂ እና በቦረና ጎሣዎች መካከል በተነሳ ከፍተኛ ግጭት በዛሬው ዕለት ደን እንደተቃጠለ ዛሬ ማምሻውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ጠቆሙ።
በጉጂ እና በቦረና ጎሣዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እየተካረረ መጥቶ፣ የሁለቱም ጎሣዎች ታጣቂዎች ፍጥጫ ላይ እንደነበሩ ለማወቅ ችለናል።
ግጭቱ የተከሰተው ዘላን (አርብቶ አደር) በሆኑት በሁለቱ ጎሣዎች መካከል ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት የጉጂ ዘላኖች የቦረናዎችን ደን (ጫካ) አቃጥለዋል።
ሁለቱም ጎሣዎች የሚኖሩበት አካባቢ ጥቅጥቅ ያለ ደን ሲሆን፣ መሣሪያ የታጠቁትንም ሆነ ሌሎችን በቀላሉ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ አካባቢውን የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ።
አለመግባባቱ የተፈጠረው የኢህአዴግ መንግሥት ጉጂዎችን እና ቦረናዎችን በጎጥና በዞን በመከፋፈሉ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ተወላጅ "ኢህአዴግ ፀቡ እንደሚፈጠር ቀደም ብሎ በማወቁ የፌዴራል ፖሊሶችን በቦታው አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም፤ ግጭቱ ተባብሶ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እንደ መንግሥት ሊወስድ የሚገባውን እርምጃ አልወሰደም" ሲሉ የኢህአዴግን መንግሥት ኮንነዋል።
እኚሁ የአካባቢው ተወላጅ አክለውም "ከዚህ በፊት በጉጂ እና በደራፉ ጎሣዎች መካከል በተከሰተ የድንበር ግጭት በላውንቸር ሳይቀር ተታኩሰው በርካታ የሰው ሕይወት ከመጥፋቱም በላይ በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። እንግዲህ አንድ 'ለህዝብ ቆሜአለሁ' የሚል መንግሥት እንዲህ ያለውን ተደጋጋሚ ግጭት ቀድሞ ማቆም እየቻለ ዝም ብሎ ማየቱ የሚያስወነጅለው ከመሆኑም በላይ ጎሣዎቹን አውቆ እያጣላቸው እንደሆነ በቂ ማስረጃ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በነገው ዕለት ተጨማሪ እና ጠለቅ ያለ ዘገባ ለማቅረብ ጥረት እናደርጋለን።



