Ethiopia Zare (እሁድ ግንቦት 23 ቀን 2001 ዓ.ም. May 31, 2009)፦ በኢትዮጵያ ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶችንና መንደሮችን በመገንባት እና እነዚህንም ቤቶችና መንደሮች በመሸጥ ተግባር የተሠማራው “አያት የመኖሪያ ቤቶችና መንደሮች ግንባታ አክሲዮን ኩባንያ”፤ ለዓመታት በቋሚና በኮንትራት ቀጥሮ ሲያሠራቸው የቆየውን ሠራተኞቹን ያሰናበተ መሆኑን አስታወቀ።

 

ኩባንያው በሺህ የሚቆጠሩ የቢሮ እና የመስክ ሠራተኞች የነበሩት ሲሆን፣ በርካቶቹን “ሥራው የሚያዋጣ ሆኖ አልተገኘም፣ ገቢዬ ቀዝቅዟል …” በሚል ምክንያት የአገልግሎት ድርሻቸውን በመክፈል ከዓመት በፊት ያሰናበተ መሆኑ ይታወቃል። ከሣምንት በፊት ለቀሪ የምሕንድስና ባለሙያዎቹ፣ የጽ/ቤትና የጥበቃ ሠራተኞቹ የስንብት ደብዳቤ የጻፈው አያት ኩባንያ፤ “ከግንቦት 18 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ በሠራተኛው እና በኩባንያው መካከል የነበረው የሥራ ውል የተቋረጠ መሆኑን አሳውቃለሁ …” የሚል ቃል በደብዳቤው ላይ አሥፍሯል። ይሄንኑ ደብዳዳቤ ተንተርሶ የተገኘው መረጃም ኩባንያው የምሕንድስና ባለሙያዎችን እና የጽ/ቤት ሠራተኛቹን ጨምሮ ከ300 የሚልቁ ሠራተኞቹን ነው ያሰናበተ መሆኑን ያመለከተው።

 

ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንዳሉት ከሆነ አያት ኩባንያ፤ የገነባቸው የመኖሪያ መንደሮችና ቤቶች ተከራይ በማጣታቸው፣ እየገነባቸው የሚገኘውም ተቋማት በሲሚንቶና በሌሎች የህንፃ መሣሪያዎቹ ዕጥረት ግንባታቸው በመስተጓጎሉ ለከፋ ኪሣራ ተዳርጓል።

 

ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ እስከ 2001 ዓ.ም. ሚያዝያ ወር ድረስም ለሠራተኞቹ ከነበረው ካፒታል ወጪ እያደረገ ወርሃዊ ደምወዝ ሲከፍል ቆይቷል። ምንጮቹ አክለው እንዳሉት አያት ከእንግዲህ ሠራተኞቹን ማስተዳደር አልቻለም። ስለዚህም የአያሌ ቤተሰብ ኃላፊ ለሆኑት አባወራዎች … መጠነኛ የአገልግሎት ክፍያ በመስጠት መበተኑን ለማወቅ ተችሏል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!