የፖሊሶች ግምገማ ያለውጤት ተበተነ
Ethiopia Zare (ዓርብ ሰኔ 12 ቀን 2001 ዓ.ም. June 19, 2009)፦ በጦላይ እና በሌሎች ማሠልጠኛ ጣቢያዎች ለ15 ቀናት ሲደረግ የቆየው የአዲስ አበባ ፖሊሶች ግምገማ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ያለምንም ውጤት መበተኑን የአዲስ አበባ ምንጮቻችን ገለጹ።
እራስን በማጋለጥ የሚለውን የኢህአዲግን የግምገማ ስልት የተከተለውና ከጅምሩ ጤናማ መንፈሥ ያልነበረው ግምገማ ፖሊሶቹ እንደገለፁት የበላይና የበታች ተብሎ መከባበር ያልነበረበት፣ አባላቱ ራሳቸውን፣ ሌላውንም ለማጋለጥ ያልሰነፉበት፣ በንቅዘት መኖራቸውን የመሰከሩበት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአዲስ አበባ ፖሊሶችን በአልታዘዝም ባይነት በማስወገድ ከሌላ ክልል የፖሊስ አባላትን አስመጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ፖሊሶች ከ10 ብር ጀምሮ በጉቦና ሲያመችም አምሽተው ሰውን በመደብደብ ከኪሱ ገንዘብ በመውሰድ፣ መሣሪያቸውን ሸጠው በመሰወር፣ … ወንጀል መሰማራታቸው በግምገማው ተወስቷል። አባላቱም በግምገማው ይህንኑ ድርጊታቸውን ሳያፍሩ ከመናገራቸውም በላይ “ደሞዛችን ሊያኖረን አልቻለም” የሚል ምክንያትም ሲሰጡ መደመጣቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል።
አለቃቸውን ደብድበው ገንዘብና መሣሪያውን ሊቀሙት እንደነበር የገለጹት ፖሊሶች፤ አለቅየው መሣሪያው ሽንት ቤት ገብቶ እንደጠፋበት ተናገሮ የነበር ሲሆን፤ በግምገማው ወቅት በመጋለጣቸው ሁሉም ከሥራ ተባረዋል። ግምገማው ከፖሊሶች ወደ ኃላፊዎች የተሸጋገረ ሲሆን፣ ከተራ ፖሊሶች ባላነሰ ጥፋት ማጥፋታቸውን አምነው፣ ለሁሉም ይቅርታ ጠይቀዋል።
የግምገማው ስብሰባ አዲስ አበባ መደረግ ሲገባው በጦላይ ለምን ተደረገ የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ባያገኙም፤ እስካሁን ለደረሰው ጥፋትና በኅብረተሰቡ ላይ ለደረሰው የሞራልና የሰብዕና ጉዳት ኃላፊነቱን የሚወስደው ማነው ለሚሉ ጥያቄዎች በግምገማው ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ከምንጮቻችን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።



