ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ከ500 የሚበልጡት እንደሚባረሩ ተገለጸ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሰኔ 27 ቀን 2001 ዓ.ም. July 4, 2009)፦ በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ከተካሄደው 3ኛ ዙር የሥነ-ምግባር ነክ ግምገማ በኋላ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ የፖሊስ ሠራዊት ባለደረቦች መካከል ከ500 የሚበልጡት “ይባረራሉ፣ በሂስና በግለ-ሂሱ መድረክ ወንጀል ስለመፈጸማቸው ያመኑትና ምስክር የቆመባቸው ፖሊሶች የክስ ፋይል ይከፈትባቸዋል” ተባለ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ አስተዳደር ምንጮች እንደገለጹት የጦላዩን የግምገማ መድረክ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ሊባረሩና በወንጀል ፈፃሚነት ጥፋት ወደ ፍ/ቤት ቀርበው ክስ የሚመሰረትባቸው አባሎች ቁጥር ከ500 የሚበልጥ ነው።
ከየካ፣ ከኮልፌ፣ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ከአዲስ ከተማ፣ ከአቃቂ ቃሊቲ፣ ከአራዳና ከጉለሌ ክ/ከተማዎች ከ80-100 የሚጠጉ የፖሊስ ባልደረቦች የወንጀል ጥፋት እና የሥነ ምግቦር ጉድለት ተገኝቶባቸዋል፤ በጦላዩ የ3ኛ ዙር ግምገማ ወቅት ብዙዎች ተገምጋሚ ፖሊሶች ከዚህ ቀደም የተለመዱ ኢሕአዴጋዊ ባሕርይ ነው የሚሉትን ግምገማ በመሰላቸት እና ከንዝንዝ ለመዳን በማለት፤ ያላጠፉትን ጥፋት እንዳጠፉ፣ ያልሠሩትን ወንጀል እንደሠሩ አድርገው በማመናቸው ወይም አጋነው በማቅረባቸው፤ የራሳቸው ቃል እና የእማኞች ምስክርነት ተዳምሮ “ክስ ይመሰርትባቸዋል” መባሉ አስደንግጦአቸዋል።
ይሁን እንጂ ይህ ከግምገማው ንዝንዝ ለማምለጥ በሚል ያላጠፉትን ጥፋት “አጥፍቼአለሁ…” ማለቱ እያስከተለ ያለውን መዘዝ የተገነዘቡ የ2ኛ እና የ3ኛ ዙር የጦላይ ግምገማ ታዳሚዎች፤ ከገምጋሚዎቻቸው ጋር “በደሞዝ ማነስና በእረፍት እጦት ከመቸገራችን በቀር ያጠፋነው ጥፋት የለም” በማለት ሲሟገቱ ተስተውለዋል። አንዳንዶቹም አዛዦቻቸውንና ገምጋሚዎቻቸውን በአጥፊነት ወንጅለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ትንሽ የማይባሉ የፖሊስ ባልደረቦች ከሞባይል ንጥቂያ ጀምሮ በአስገድዶ መድፈር፣ በቅሚያና በስርቆት ወንጀል ተሰማርተው መገኘታቸውና የዚሁም ድርጊት ተባብሶ መቀጠል የመንግስቱን የበላይ ሰዎች ማሳሰቡ የአደባባይ እውነት ከሆነ ሰንብቷል።



