Ethiopia Zare weekly news digest, week 12, 2012 Ethiopian calendar

ከኅዳር 15 -21 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አሥራ ሁለተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከኅዳር 15 - 21 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ሳምንቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እንደ አዳዲስ የሚታዩ የተለያዩ ክስተቶችን አስተናግዶ ያለፈ ነው። ክስተቶቹ አላፊ ናቸው ተብለው የሚታለፉ ሳይሆን፤ በቀጣይ አነጋጋሪ ሆነው የሚቀጥሉ፣ መጨረሻው ምን ይሆን? የሚል ጥያቄ የጫሩ ናቸው ማለት ይቻላል። ከብልጽግና ፓርቲ የምሥረታ ሒደት ጋር ተያይዞ አዳዲስ ክዋኔዎች የተስተዋሉበት ሳምንት መሆኑ አንዱ ነው። ከሕወሓት በስተቀር ሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች ከብልጽግና ፓርቲ ጋር “ወደፊት!” በሚል ማረጋገጫ የሠጡበትና ይህንንም በየድርጅቶቻቸው በጠቅላላ ጉባዔ በአዲሱ ፓርቲ ምሥረታ ላይ ወስነው ያጠናቀቁበትና በሕብረት የስምምነት ፊርማ ያሳረፉበት ሳምንት ነበር። እንዲህ ካለው ሒደት በተቃራኒ የቆመው ሕወሓት ደግሞ የተቃውሞ ድምፁን በይበልጥ ያሰማበት ሳምንት ነው።

ሕወሓት ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ላለመቀላቀል እንደምክንያት የሚጠቅሳቸውን ጉዳዮች በድርጅቱ (ሕወሓት) ከፍተኛ አመራሮች በተደጋጋሚ መገለጹ ሳምንቱን ለየት ሊያደርገው ይችላል። በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ የተሰማው ሌላ ዜና ደግሞ የብዙዎችን ትኩረት ከመሳብ አልፎ ያልተገመተ የሚባል ነው። ይህ ዜና የአገሪቱ ፖለቲካና የፖለቲከኞች ጉዳይ ያልተፈቱ ብዙ ቋጠሮዎች ያሉት መኾኑን የጠቆመም ነው። “ቲም ለማ” የሚባለውንና የለውጡ ፊት አውራሪ በመኾን የሚጠቀሰውን ቡድን በመምራት የሚጠቀሱት አቶ ለማ መገርሳ፤ ከዶክተር ዐቢይ አሕመድ መደመር ፍልስፍና ተቃራኒ መቆማቸውን የሚያመላክተው አጭር ቃለምልልሳቸው የሰሞኑ ወፍራም ወሬ ሆኗል። ይህ ብቻ ሳይሆን አቶ ለማ ከሰሞኑ ብዙ እየተባለለት ያለውን የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውሕደት የማይስማሙበት መኾኑን በይፋ የገለጹበት ሳምንት ነው። ከእርሳቸው አንደበት ወጣ የተባለው ቃልና ይህንንም ተከትሎ እየተሠጡ ያሉት አስተያየቶችን ማሕበራዊ ድረገጾች ትኩስ መወያያ አጀንዳ አድርገውታል።

በዚህ ሳምንት እንደ አንድ አገራዊ ፖለቲካዊ ጉዳይ የሚቆጠረው ሌላው ክንውን ምርጫ ቦርድ በጠራው የፖለቲካ ድርጅቶች የምክክር መድረክ ጥያቄ አለን ያሉ ወገኖች ባነሱት ጥያቄ ሰበብ የታቀደው ስብሰባ ሳይጀመር መበተኑ ነው።

ከፖለቲካ ጉዳዮች ባሻገር ያሳለፍነውን ሳምንት በይበልጥ ከምናስታውስባቸው ክስተቶች ውስጥ በቀናት ልዩነት፤ በኦሮሚያ ክልል ብቻ 32 የሚሆኑ ዜጐችን ያጠፉ የትራፊክ አደጋዎች የተስተናገዱበት መኾኑ ነው።

በአዲስ አበባ ደግሞ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ታዳጊ ተማሪዎች ከምገባ በኋላ መታወክ ደረሰባቸው የሚለው ዜና በሳምንቱ አነጋጋሪ ክስተቶች ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የሚካተት ነው። ከቢዝነስ ዜናዎች የአገሪቱ የግል ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የ2011 በጀት ዓመት የፋይናንስ ሪፖርታቸውን በተከታታይ እያቀረቡ መኾኑ ጐልቶ የሚጠቀስ ነው።

ብልጽግና ፓርቲ ሰሞናዊ ጉዞ

ከኢሕአዴግ እኅት ፓርቲዎች ከሚባሉት አራቱ ድርጅቶች ሦስቱ፣ እንዲሁም ለዓመታት አጋር በመባል የሚታወቁት አምስቱ ድርጅቶች የውሕደት አስፈላጊነትን በማመን በአዲስ ስያሜ ወደ መደራጀት መግባት እርግጥ መኾኑን የሚያመለክቱ ውሣኔዎችን አሳልፈዋል። ውሳኔያቸውን ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ድርጅቶች መሪዎች የብልጽግና ፓርቲን እውን ያደረጉበትን የስምምነት ሰነድ ኅዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ፈርመዋል።

ሕወሓት በዚህ ስብስብ ውስጥ ለመግባት አልፈቀደም። ወይም የአዲሱ ፓርቲ ምስረታና የውሕደት ጉዳይ ላይ የማልስማማቸው ጉዳዮች አሉ ብሎ ከዳር ኾኖ ተቃውሞውን እያሰማ ነው። ብልጽግና ፓርቲን ለመቀላቀል ስምንቱ ድርጅቶች እንዲህ ባለው ስምምነት ፀንተው የብልጽግና ፓርቲን ቀጣይ ጉዞ በጋራ ለመራመድ የጋራ ስምምነታቸውን በፊርማቸው ሲያረጋግጡ፤ ሕወሓት በበኩሉ እንዲህ ማድረግ ችግር አለው እያለ ነው። የብልጽግና ፓርቲ ምሥረታ እውን መኾኑን የሚያረጋግጡ እውነታዎች በተከታታይ ከተሰሙ በኋላ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የሕወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በሠጡት መግለጫ፤ ብልጽግና ፓርቲን ለመመሥረት እየተሔደበት ያለው መንገድ ሕጋዊ አይደለም ብለዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የብልጽግና ፓርቲ ምስረታ ድርጅቶችን የሚያፈርስ በመኾኑ ጭምር ከስሰው፤ ከዚህ አንፃር ሕወሓትን ማክሰም እንደማይችል ገልጸዋል። በብልጽግና ፓርቲ ምሥረታ በተደጋጋሚ ለተለያዩ ሚዲያዎች አስተያየታቸውን በመሥጠት ቀዳሚ የኾኑት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ አቶ ጌታቸው ረዳም የዶ/ር ደብረጽዮንን ሐሳብ የሚያጠናክር ቃለምልልሶችን ሠጥተዋል። የአዲሱ ፓርቲ የምሥረታ ሒደት ሕጋዊ የድርጅቱን አካሄድ የተከተለ አይደለም በማለት ይኮንናሉ። ሒደቱ ሕጋዊ ካለመኾኑም በላይ፤ አዲሱ ፓርቲ አኀዳዊ ሥርዓትን ለመመሥረት እየተንደረደረ ያለና አገሪቱን ከአራት ኪሎ ለማዘዝ ቆርጦ የተነሳ አድርገው ስለውታል። የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚነካ ሁሉ ስለመኾኑንም ጥርጣሬ የሌላቸው እንደሆነ ሲናገሩም ተሰምተዋል። እንዲህ ያለው የሕወሓት ባለሥልጣናት አስተያየት ግን ትክክል ስላለመኾኑ የአዲሱ ፓርቲ የተለያዩ አመራሮች የተለያዩ መረጃዎችን በማቅረብ ሲገልጹ ሰንብተዋል።

ለሕወሓት አመራሮች የብልጽግና ፓርቲ የምሥረታ ሒደት ትክክል አይደለም የሚለውን ምላሽ ለመሥጠት በሚመስል መልኩ ምላሻቸውን ከሠጡት ውስጥ አንዱ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው።

አቶ ንጉሡ የዶ/ር ደብረናጽዮን መግለጫ በሠጡ ማግስት እንደገለጹት የሚባለው ሁሉ ትክክል አለመኾኑን ነው። ውሕደቱን በተመለከተ ያልተወያየንበት ነው የሚለውንም ትክክል ያለመኾኑንና በየደረጃው ለድርጅቶቹ አመራሮች ተሠጥቶ የተመከረበት እንደሆነ አስረጅ ያሉትን እውነታቸውን በማስደገፍ ምላሽ ሠጥተዋል።

የፓርቲው ምስረታ እውን እየኾነ መምጣቱንና እንደተባለው ሕግን ያልተከተለ አካሔድ እንዳልነበር የሚያጠናክር መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብልጽግና ፓርት የምሥረታ ሒደት ሕግን ጠብቆ የተከናወነ መኾኑን አጽንዖት ሠጥተው ተናግረዋል። አያይዘውም እኛን የሚቃወሙን አንዳንድ ኃይሎች አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ አኀዳዊ ሥርዓትን የሚያመጣ የፌዴራል ሥርዓትን የሚያጠፋ ነው በሚል የሚነገረው አሉባልታ እንደኾነና ትክክል ያልኾነ መኾኑን አስረድተዋል። እንዲያውም እንዲህ ያለውን አሉባልታ የሚያራግቡ አካላት ያድምጡኝ ብለው የተናገሩት፤

“ብልጽግና ፓርቲ በግልጽ እንዳስቀመጥነው ሕብረ ብሔራዊት ፌዴራላዊት ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን የሚያጠናክር፣ የሚገነባ እንጂ የማያፈርስ መኾኑን በንግግር ብቻ ሳይሆን በፓርቲው ፕሮግራም ውስጥ የተካተተ ነው” በማለት ነው።

ብልጽግና ፓርቲን በመክሰስ ሳይሆን አማራጭ በማምጣት እንዲሞግቷቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ሐሳብ ይዘው እንዲቀርቡ ጥሪ ያስተላለፉት ዶ/ር ዐቢይ፤ የብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምድ ስለመኾኑም ያብራሩበት ሳምንት ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንም በዚሁ ውሕደት ዙሪያ ተመሳሳይ የኾነ ሐሳባቸውን በዚህ ሳምንት ከሰነዘሩት ውስጥ ሌላኛው ከፍተኛ አመራር በመኾን ይጠቀሳሉ። ለውጡና አዲሱ ውሕድ ፓርቲ አግላይ አለመኾኑን፤ በተለይ ትግራይን ያገለለ ነው በሚል የሚቀነቀው ፕሮፖጋንዳ ከእውነት የራቀ ስለመኾኑ የተለያዩ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ሰፊ ማብራሪያ የሠጡበት ሳምንት ነበር። “ለውጡን ያልተቀበለው በተለያዩ መልክ የለውጡ አካሔድ ያልጣመው በመሰባሰብ ሁኔታዎች በትግራይ ሕዝብ ላይ ያንዣበበ እንደሆነ፤ ጥቃትና አደጋ እንደሚደርስበት፤ ኾን ተብሎ የማዘጋጀትና በዚያ ላይ ተጽእኖ የመፍጠር ሥራዎች ተሠርተዋል” ይላሉ።

አያይዘውም “ከዚህም በላይ ሕወሓትን አግልሎ የት ሊደረስ? ሁሉም ተያይዞ እንዲሻገር ያስፈልጋል” በማለት አሁን እየተካሔደ ያለው የለውጥና የውሕደት ሒደት ሁሉንም የማሳተፍ ፍጹም ፍላጐት ያለው መኾኑን አስረድተዋል። ለውጡ እስከ ዛሬ የነበሩት መልካም ነገሮች በማስቀጠል እንደ ግድፈት የሚቆጠሩትን ደግሞ በማስቀረት የሚጓዝ ስለመኾኑ አስረድተዋል።

ከውሕደቱ እንቅስቃሴ የመገለል ሁኔታ አለ የሚባለው ነገር ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሠጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ ቅሬታ አለን በሚል ከዚህ ወደ ትግራይ በመሄድ፣ አዲስ አበባም ቢሆን፣ መቀሌም ቢሆን በሁሉም በአገሩ ሆኖ መታገል ስሜት መገለጽ፣ መቃወም እየተቻለ፤ እንዲህ እየተሰባሰቡ ለውጡን በተለያየ መልክ የሚገልጹ የተሳሳቱ አካሄዶች በተወሰኑ ኢንዲቪዥዋልስ (ወገኖች) የሚከናወን ስለመኾኑ ጠቅሰዋል። ይህ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው አስታውሰው፤ ያኛው ደግሞ ለውጥ የተባለ ነገር የተለያየ ስም እየወጣለት ውሕደቱ የትግራይን ሕዝብ ሊጨፈልቅ ነው በሚል ያልሆነ ነገር ማቀንቀን ያልተገባ ስለመኾኑ ተናግረዋል። ውሕደቱ ብሔር ብሔረሰብን ሊጨፈልቅ ነው፣ አኀዳዊ ሥርዓት ሊመሠረት ነው በሚልና የተለያየ ስም የሚሠጠውም ነገር ፈጽሞ ስሕተት ነው በማለት፤ የብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም በመያዝ የሚጓዝ፣ አሁንም ለሁሉም በሩን ክፍት በማድረግ በአሳታፊነት የሚጓዝ መኾኑን አስረድተዋል።

ሕወሓት ግን ከብልጽግና ፓርቲ መቀላቀሉም አለመቀላቀልም መብት እንዳለው ዶክተር ደብረጽዮንና አቶ ጌታቸው ረዳ በጉዳዩ ላይ በሠጡት መግለጫ ያንጸባረቁ ሲሆን፣ ይህ አገላለፃቸው የራሳቸውን ፓርቲ ለማቋቋም መብት እንዳላቸው የሚያመላክት እንደኾነ የሚጠቁም ነው በሚል የሚገልጹ አሉ። ፌዴራሊስቶች የሚባሉ ወገኖችን በማሰባሰብና አንድ ፓርቲ በመቋቋም ብልጽግናን ለመገዳደር ያቀዱ ስለመኾናቸው የሚያሳይ ነው የሚሉም አሉ።

ለዚህም ከፌዴራሊስት የሚያቀነቅኑ ፓርቲዎችን በመጋበዝ በቅርቡ መቀሌ ላይ አንድ ስብሰባ ለማድረግ መወሰናቸው አንድ ማሳያ ነው ይላሉ። ይህ የሕወሓት ጥረት የት ሊያደርሰው እንደሚችል መገመት ባይቻልም፤ በብልጽግና ፓርቲ ጉዳይ እንዲሁም በሕወሓት ጉዳይ ላይ ለመምከር የሕወሓት ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚካሔድ ግን ዶ/ር ደብረጽዮን አረጋግጠዋል። ይህ ስብሰባ የወደፊቱን የሕወሓት አቅጣጫ መቋጫ ይሠጠዋል የሚለው እምነት ግን የብዙዎች ሆኗል። ከትግራይ የሚሠራጩ ሚዲያዎች የሚያስተናግዷቸው አስተያየቶችና የውይይት መድረኮች በሙሉ ውሕደቱን የሚቃወሙ ኾነው ሰንብተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ጉዳይ እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች እያስተናገደና ከግራና ቀኝ የሚሠጡ አስተያየቶች አሁንም በቀጠሉት ሁኔታ ግን፤ በብልጽግና ፓርቲ ስር መሰባሰባቸውን በአወንታዊነት የተቀበሉ አመራሮች ሥራቸውን ቀጥለዋል።

ቅዳሜ ኅዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም. የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊዎች በወቅታዊ ሁኔታዎችና በፓርቲው ሥራዎች እቅድ ላይ እየተወያዩ መኾኑ ከተነገረና የብልጽግና ፓርቲው ጽ/ቤትና የክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊዎች በፓርቲ ጽ/ቤት ላይ እየመከሩ ስለመኾናቸው ተደምጧል። በኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውሕደት በተፈጠረው የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ ሁሉም ሕብረ ብሔራዊ ውሕድ ፓርቲውን የተቀላቀሉ ፓርቲዎች ጽ/ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል ተብሏል። ይህ በሆነ ማግስት ደግሞ በኢሕአዴግ ስር ከነበሩት ዘጠኙ ድርጅቶች (አጋሮችን ጨምሮ) የስምንቱ ድርጅቶች መሪዎች የብልጽግና ፓርቲን ውሕደት የሚያረጋግጥ ፊርማቸውን አኑረዋል። በዚህ የፊርማ ሥርዓት ላይ ዶ/ር ዐቢይ ብልጽግና በእውቀትና በእውነት ላይ የተመሠረተ ፓርቲ መኾኑን በመግለጽ፤ አገሪቱን የሚያሻግር ፕሮግራም ያለው፤ ለዚህም የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ አዛጋጅቶ ይፋ ማድረጉን በማሳወቅ፤ ይህንን ፕሮግራም ሕዝብ ሊያዳብረው እንደሚችል ገልጸዋል። (ኢዛ)

ለማ ወዴት?

ኅዳር 20 እኩለ ሌሊት አካባቢ የተሰማ አንድ ዜና ለብዙዎች አምነው ለመቀበል የተቸገሩት ነበር ማለት ይቻላል። የዜናው ምንጭ ደግሞ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ሲሆን፣ ያልተጠበቀ ነው የተባለው ዜና፤ አቶ ለማ መገርሳ የመደመር ፍልስፍና አቀንቃኝ ስላለመኾናቸውና ይህ ፍልስፍና ለእርሳቸው ጭምር ያልገባቸው መኾኑን የገለጹበት ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውሕደትም ጊዜውን ያልጠበቀ ነው በማለት አጠንክረው የተናገሩት አቶ ለማ፤ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውሕደትም ችኮላ የተሞላበት መኾኑን ገልጸዋል።

“በችኮላ ማዋሐዱና የተሔደበት መንገድ ደስ አላለኝም” ያሉት አቶ ለማ፤ “በተለይ አሁን ቀድሞ ሊሠሩ የሚገባቸው ጉዳዮች እያሉ ውሕደትን ማስቀደሙ ተገቢ አለመሆንም ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ የተለያዩ ሐሳቦች ተንሸራሽረው በዚህ ጉዳይ ላይ እውቀት ያላቸው ሰዎች ተሳትፈውበት የሕዝብ አመለካከት ተሰብስቦ ሕዝቡ በሙሉ እምነት ተቀብሎት ሥራ ላይ ማዋል ሲቻል፤ አንዱን ነገር ሳይፈቱ መደራረቡ ጥርጣሬ ውስጥ አስገብቶኛል” የሚል ቃላቸውን ሠጥተዋል። ይህ ሐሳብ እንዲዘገይ በተናጠልም ሆነ በጋራ ለምኛለሁ፤ ግን አልተደመጥኩም የሚል ቅሬታቸውን ያንጸባረቁበት ነው።

በተለይ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን ለማዋሐድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደማይደግፉት ያመለከቱት አቶ ለማ፤ ለዚህ ልዩነታቸው ከጠቀሱዋቸው ምክንያቶች አንዱ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ላቀረበልን ታላላቅ ጥያቄዎች ቀድሚያ መልስ መሥጠት ስለሚያስፈልግ ነው የሚል ነው። ይህንንም “እኛ የኦሮሞ አመራር አባላት የኦሮሞ ሕዝብ አምኖ ያቀረበልን ትላልቅ ጥያቄዎች ስላሉ፤ ለነሱ መጀመሪያ መልስ መሥጠት አለበት” የሚል አመለካከት አላቸው።

“እነዚህን ጥያቄዎች እንመልስላችኋለን ብለን ቃል ገብተናል። ሕዝባችን ይህንን ጥያቄ ያቀረበልን የትናንቱን ኦሕዴድ ስም ለውጠንለት ስሙን ለውጠን ኦዴፓ ካልን በኋላ ነው። ስለዚህ ሕዝቡ አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት ብሎ የሠጠው ለአገራዊ ፓርቲው ሳይሆን ለኦዴፓ ነው። ስለዚህ የሕዝቡን ጥያቄ ሳንመልስ ይህንን ማድረግ ትክክል አይደለም። እምነት ማጉደል ይሆናል። እናም ጥያቄዎቹን ቆጥሮ እንደሠጠን መመለስ ይገባል” የሚል አቋም አላቸው።

አቶ ለማ መገርሳ መደመርና እሳቸው የማይስማሙ ስለመኾኑ ገልጸዋል። እንዲያውም አልገባኝም እስከማለት ደርሰዋል። ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባሉ ብለው የሚያምኑት የኑሮ ውድነት ላይ መሥራት አንዱ ነው። የአገሪቱ ፀጥታ ሁኔታ ሁለተኛው ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ በቀጣዩ ምርጫ ዙሪያ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ትኩረት መሠጠት አለበት የሚል እንደሆነ ገልጸዋል። ይህንን ልዩነታቸውን ይዘው አሁንም እንደሚሞግቱ ተጨማሪ መረጃዎችንም እንደሚሠጡ ገልጸዋል።

አቶ ለማ በዚህ ደረጃ ከዶክተር ዐቢይ ይለያሉ ብሎ ለመገመት ብዙዎች የተቸገሩበት ነበር። በተለይ ልዩነት ቢኖር እንኳን እስካሁን ቆይቶ በዚህ ሰዓት ለምን? የሚል ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፤ በዚህ የአቶ ለማ ቃለምልልስ ኦፊሻሊ ምላሽ የሠጡት የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ሲሆኑ፤ በፓርቲው ምስረታና በመደመር እሳቤ ላይ ማብራሪያ ሠጥተው በፕሮግራሙ ላይ ለመወያየትም በሩ ክፍት መኾኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ዜና በኋላ በየአቅጣጫው የሚሠነዘሩ አስተያየቶች የተለያዩና በርካቶች ናቸው። የአቶ ለማ እንዲህ ያለ አቋም ላይ መድረስ ለምን በዚህ ሰዓት እንዲገለጽ ተፈለገ ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ፤ ልዩነቱ ዛሬ ያልተጀመረ፣ የቆየ ነው የሚል አመለካከትን የሚያንጸባርቅ መልእክቶች ታይተዋል። ብዙዎች በለውጡ ሒደት የአቶ ለማን ቀዳሚ ውለታ ያልዘነጉ አስተያየቶች ጐልተው ታይተዋል። የዚያኑ ያህል ለምን አቶ ለማ? ያሉም አሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን አቶ ለማ የፈለገ ልዩነት ቢኖራቸው የለውጡ ቀኝ እጅ ነበሩና የተለየ ሐሳብ ይዘው ብቅ ማለታቸው መብታቸው እንደሆነ የሚገልጹም አልታጡም። በተለይ እኔንና ዐቢይን የሚለየን ሞት ነው በማለት ሲገልጹ የነበሩት አቶ ለማና ብልጽግና ፓርቲ እንዴት ይጓዛሉ? የሚለው ጥያቄ በእንጥልጥል ላይ ነው። (ኢዛ)

ምርጫ ቦርድና ሳይጀመር በፓርቲዎች ተቃውሞ የተቋረጠው ውይይት

የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው ረቂቅ መመሪያ ላይ ለመወያየት የታቀደው ስብሰባ ሳይካሄድ ቀርቷል። በዚህ ረቂቅ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ እንዲኾኑ ከምርጫ ቦርድ የተደረገውን ጥሪ ተከትሎ ስብሰባው በሚካሔድበት (ኅዳር 20 ቀን 2012 ዓ.ም.) የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችና መሪዎች ቢገኙም፤ በዕለቱ ለመካሔድ የታቀደውን ለማከናወን ሳይችል የቀረው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ አዋጅ ከመጽደቁ በፊትና በረቂቅ ደረጃ እያለ በአዋጁ እንዲካተትልን ጠይቀን፤ ይህ ተፈጻሚ ሳይሆንልን ቀርቷል የሚል አቋም ይዘው በመቅረባቸው ነው።

ስለዚህ የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ አዋጅ ለማስፈጸም በወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ ከመወያየታችን በፊት በአዋጁ ላይ ያነሳነው ጥያቄ ሊመለስልን ይገባል በሚል ያነሱት ጥያቄ፤ በዕለቱ ውይይት ሊደረግበት የነበረው አጀንዳ ሳይታይ ሊበተን ችሏል።

በዋናው አዋጅ ላይ ግብአት ኾኖ እንዲካተት ያቀረብነው ሐሳብ ግብአት ኾኖ እንዲካተት ሳይደረግ፤ እንደገና በዚህ ደንብ ላይ ተወያይተን ልናቀርብና እንዲካተት የምንሻው ሐሳብም ሊካተትልን ይችላል የሚል እምነት በማጣታቸው በዕለቱ አጀንዳ ላይ ለመወያየት አለመፈለጋቸውን ጭምር ገልጸዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን አንዳንዶች እንዲያውም በምርጫ ቦርዱ ላይ እምነት የለንም የሚል ክስ ሰንዝረዋል። ስብሰባው ሳይጀመር ከተበተነ በኋላ አስተያየት የሠጡት ወ/ሮ ብርቱካን፤ አዋጁ የጸደቀ በመኾኑ ምርጫ ቦርድ ከዚህ በኋላ በአዋጁ ላይ ምንም ማድረግ የማይችል መኾኑን ገልጸው፤ ሆኖም አሁንም በአዋጁ ላይ ሐሳብ ካላቸው በጽሑፍ ይቅረብ ብለዋል።

እንዲህ ያሉ ተቃውሞዎችና ሐሳቦች የተለመዱና በምርጫ ወቅት የሚጠበቁ ናቸው ያሉት ወይዘሪት ብርቱካን፤ ሆኖም ሁኔታዎቹ በተደገሙ ወቅት ሥራ ላይ እንቅፋት ሊኾኑ እንደማይችሉ ግን ሥጋታቸውን ሳይገልጹ አላለፉም።

ምርጫውን ለማካሄድ እየተዘጋጀን ነው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢዋ፤ እንዲህ ዐይነት ነገሮችን በመነጋገር ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ