Ethiopia Zare's weekly news digest, week 31st, 2012 Ethiopian calendar

ከመጋቢት 28 - ሚያዝያ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሠላሳ አንደኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከመጋቢት 28 - ሚያዝያ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ያሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥጋት ጋር በተያያዘ በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች። አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።

ይህ አዋጅ ለአምስት ወር የሚቆይ ነው። ዝርዝር የአዋጁ ማስፈፀሚያዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት እየወጣ ይፋ እንደሚደረግ የሚገልጽ በመኾኑ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁ በሚጸድቅበት ወቅት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ፤ ይኸው ክልከላዎችን የማያመለክት በመኾኑ ነበር። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ግን የዚህን አዋጅ ዝርዝር ጉዳዮች የሚያመለክት ማስፈፀሚያ ደንብ ይፋ ተደርጓል። እንዳለፉት ጥቂት ሳምንታት ሁሉ ባሳለፍነው ሳምንትም አብዛኛዎቹ ዜናዎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዙ ናቸው። እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ድረስ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች 71 ደርሰዋል።

የሟቾች ቁጥር ደግሞ ሦስት ደርሷል። ወደ አሥር የሚኾኑት ደግሞ ማገገማቸው የተነገረበት ነው። እስካሁን በተከታታይ ከወጡ ሪፖርቶች መገንዘብ የሚችለው በየሳምንቱ ሪፖርት የሚያደርጉ የቫይረሱ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ነው። የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መንግሥት እያደረገ ካለው ጥረት ባሻገር እንደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማብራሪያ እነዚህን የመብት ገደቦች እና እርምጃዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ ዘርዝሮ ማስቀመጥ ያልተቻለው አስፈላጊ የሚኾኑት ገደቦች እና እርምጃዎች ከጊዜ ጊዜ እና በአገሪቱ ውስጥ ከቦታ ቦታ ሊለያዩ ስለሚችሉ ነው ብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፈፀም ኃላፊነትን በተለከተም የመብት ዕገዳዎቹና እርምጃዎቹ ዝርዝር ሁኔታ በየጊዜው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይወጣል። በበጎ ፍቃደኝነት የሚደረጉ መልካም ተግባራትም እየጨመሩ መምጣታቸውን በዚህ ሳምንት መታዘብ ተችሏል።

አዲስ አበባ ተወስኖ የቆየው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ አሁን በክልል ከተሞችም መሠጠት እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን፤ እስካሁን በአራት ከተሞች ይኸው ተግባር ተጀምሯል። በአዲስ አበባና በመቀሌ የቤት ለቤት ምርመራ እንደሚጀመር የተገለጸውም በዚሁ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። የዓለማችን ቁጥር አንድ አጀንዳ የኾነው የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ በሌላ ገጽታው ኢትዮጵያን የሚመለከት ነገር ወልዷል። ይህም የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም ላይ የተነጣጠረው እስከ ግድያ የደረሰ ዛቻና ተያያዥ ጉዳዮች መነጋገሪያ ኾኖ አሁንም ድረስ ቀጥሏል።

ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሳምንቱ ዐቢይ ኢኮኖሚያዊ ዜና ሊባል የሚችለው በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የሚፈጠው ኢኮኖሚያዊ ውድመት ከባድ መኾኑ በአኀዝ ጭምር የተገለጸበት መኾኑ ነው። አሁን ያለው ችግር ለወራት ከዘለቀ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኾነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሚደርስባት መኾኑ እየተነገረ ነው። በተለይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር በዚሁ ጉዳይ ላይ ጥናት በማድረግ ያወጣው ሪፖርት አደገኝነቱን በደንብ የሚያመለክት ነበር።

ኢትዮጵያ እስከ 200 ቢሊዮን ብር የሚደርሰ ጉዳት ይደርስባታልም ብሏል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በታሪክ አስመዝግቦት የማያውቀውን ኪሣራ በአራት ወር ውስጥ የማስመዝገቡ ጉዳይ ከዚሁ አገራዊ የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር የተያያዘ ነው። በአጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ ኢኮኖሚያዊ ጥቃት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ቢዝነሶች ላይ ጐልቶ እየታየ ሲሆን፤ ችግሩ ካለፈ በኋላም ለማገገምም ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል መኾኑም ከወዲሁ እየተነገረ ነው።

ኢትዮጵያ ዛሬ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እና የሰሞኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ትኩረት ያደረገውንና አንዳንድ የሳምንቱ ዜናዎችን እንደሚከተለው ቃኝታለች። መልካም ንባብ!

በጐ እጆች

በዚህ ወቅት የተለያዩ በጐ ተግባራትን እየተመለከትን ነው። በተለይ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ አብዛኛው ሳይሆን ጥቂት አከራዮች የሚያዝያን ወር የቤት ኪራይ ሙሉ በሙሉ ሲሰርዙ እየታየ ነው። አንዳንዶች ግማሽ ዋጋ እያስከፈሉ ነው።

ወቅታዊ ችግር የገባቸውና ወረርሽኙን ከአገራችን ያውጣልን ብለው ነገሩን በብርቱ ያሰቡቱ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ እስኪጠፋ ተከራዮቼን የቤት ኪራይ አልጠይቅም ያሉም ታይተዋል። ይህ መልካም ተግባር በግል አከራዮች ብቻ ሳይሆን መንግሥትም ራሱ በሚያስተዳድራቸው የኪራይ ቤቶች ላይ የኪራይ ቅናሽ አድርጓል።

ይህም ከ18 ሺሕ በላይ ቤታችን የሚያስተዳድረው የመንግሥት ቤቶች (ወይም የኪራይ ቤቶች) የሚያዝያ ወር የቤት ኪራይ ዋጋን በግማሽ መቀነሱንና የኪራይ ቤቶች ተከራዮች የሚያዝያ 2012 የኪራይ ዋጋ ግማሹን ብቻ ክፈሉ ብሏል። ይህ የድርጅቱ ውሳኔ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ የሚያሳጣው ቢኾንም፤ አሁን ካለው ሥጋት አንፃር የበኩሉን ለማድረግ በማሰብ ነው ተብሏል። (ኢዛ)

ዶክተር ቴዎድሮስና ውዝግብ

የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዋና ዳይሬክተር በመኾን እያገለገሉ ያሉት ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም እና የሚመሩት ድርጅት ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ተከፍቷል። አሜሪካንን ጨምሮ በአንዳንድ አገራት የኮሮና ወረርሽኙ እያስከተለ ያለውን ጥፋት በWHO ላይ ለማላከክም ያለመ ነው ማለት ይቻላል።

ዶ/ር ቴዎድሮስም የሠጡት ምላሽ እንዲሁም ይህንኑ ተከትሎ በየአቅጣጫው እየተንሸራሸሩ ያሉ ሐሳቦች ከሳምንቱ አነጋጋሪ ወሬዎች አንዱ ነበር። የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ግን በዶክተር ቴዎድሮስ ላይ የተከፈተውን ዘመቻ በመቃወም ከዶ/ር ቴዎድሮስ ጋር መኾናቸውን እየገለጹ ነው። ከኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጀምሮ ሌሎች የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጭምር ከዶክተር ቴዎድሮስ ጎን ነን በማለት አቋማቸውን ሲያንጸባርቁ ሰንብተዋል።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የዓለም ጤና ድርጅት ቀድሞ ማሳወቅ የነበረበትን መረጃ አልሠጠም የሚል አንደምታ ያለው አመለካከት በመያዝ፤ ዶ/ር ቴዎድሮስ ከሥልጣናቸው ይውረዱ የሚል ፊርማ እስከማሰባሰብ ተደርሷል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለቫይረሱ መስፋፋት የዓለም የጤና ድርጅት ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፤ ድርጅቱ ለቻይና ያደላ ሥራ ሠርቷል በማለት ደፍረው እስከመናገር መድረሳቸው ደግሞ ነገሩን ውስብስብ አድርጐት ሰንብቷል።

ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተከታታይ ያቀረቧቸው ወቀሳዎች የዓለም ጤና ድርጅት ቸልተኝነት ያልተገባ መሥዋዕት ተከፍሏል የሚል ጭምር ነው። ፕሬዝዳንት ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወሰደው ውሳኔን በመቃወም፤ አሜሪካ ለዓለም የጤና ድርጅት የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ለማስቀረት እስከ መዛት ደርሰዋል። የትራንፕ አቋም ከዚህም በላይ ሔዶ የዓለም ጤና ድርጅት ለቻይና ያደላ ሥራ እየሠራ ነው በማለት ጭምር ዶክተር ቴዎድሮስ ላይ ትችት ሰንዝረዋል።

ታይዋንም በዶክተር ቴዎድሮስ ላይ በይፋ ትችት ካቀረቡ አገራት መካከል አንዷ ኾናለች። እንዲህ ባለው ሁኔታ ጣት የተቀሰረባቸው ዶ/ር ቴዎድሮስ በተለይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያቀረቡትን ወቀሳ ተከትሎ በሠጡት መግለጫ “የዓለም ጤና ድርጅት አሠራር ለቻይና የወገነ እና ለወረርሽኙ ምላሽ ለመሥጠት የዘገየ ነው” በሚል የተወቀሰበት መንገድ አግባብ አለመኾኑን ብቻ ሳይሆን፤ ነገሩን ፖለቲካ አታድርጉት በማለት ትራምፕና ቢጤዎቻቸውን ውርፈዋል። የፕሬዝዳንት ትራምፕን ወቀሳና ክስ ያደረጉት “የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ፖለቲካዊ ማድረግ አይጠቅምም፤ ሊቆም ይገባል” ሲሉም ዶ/ር ቴዎድሮስ ገልጸዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት ከዘርና ቀለም በጸዳ ሁኔታ ለሁሉም ሕዝብ ቅርብ ኾኖ እየሠራ እንደሚገኝ በመግለጽም፤ አሁን የሚያስፈልገው ሁሉም በአንድነት ኾኖ ወረርሽኙን ለመከላከል በጋራ መሥራት ብቻ መኾኑን ነው። ጥቁር በመኾናቸው ብቻ ለደረሰባቸውን ጥቃት በጨዋ ደንብ ምላሽ የሠጡት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ ጥቁር በመኾናቸው እንደሚኮሩም ከሰሞኑ ገለጻዎቻቸው መሐል ሳያመላክቱ አላለፉም።

በዚህ ሰሞናዊ ውዝግብ አስተያየታቸውን ከሠጡት መካከል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይገኙበታል። እንደእርሳቸው ገለጻ ሁሉም አካላት ይሔንን ወረርሽኝ ማስቆም ላይ ቅድሚያ ሠጥተው መሥራት እንዳለባቸው፤ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ወቀሳቸውን የማቅረቢያ ሰፊ ጊዜ እንደሚኖራቸውም ተናግረው፤ የሚሻላቸው በጋራ መሥራት ነው ብለው የዓለም ጤና ድርጅት ላይ እየተሰነዘረ ያለው ወቀሳ አግባብ አለመኾኑንም አመልክተዋል።

ቫይረሱ የሚያስከትለውን አስከፊ መዘዝ ለማስቆም እንዲቻል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአንድነት ተባብሮ ለመሥራት ጊዜው አሁን መኾኑን የተናገሩት አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የቫይረሱ ሥርጭት ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር ሲነፃፀር በአፍሪካ በጣም አናሳ ቢኾንም ከቀን ወደ ቀን እያደገ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።

ቻይና በበኩሏ በዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም ላይ የተከፈተውን ግለሰብ ላይ ያነጣጠረ የዘረኝነት ጥቃት እንደምታወግዝ ያሳወቀችው በዚሁ ሳምንት ነበር። የተከፈተውን የዘረኝነት ጥቃት ዘመቻ ቻይና አጥብቃ እንደምታወግዝ ቻይና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ በኩል በመግለጽ ከዶክተር ቴዎድሮስ ጋር ስለመኾኗ አሳውቃለች።

በዶ/ር ቴዎድሮስ የአመራር ዘመን የዓለም የጤና ድርጅት የአገራትን የጤና ሥርዓት የሚያሻሽሉ ሥራዎችን በመተግበር፣ ከባድ ዓለም አቀፍ ወረርሽኞችን ለመከላከል ፈጣን ምላሽ በመሥጠት ስለመሥራታቸውም ይኸው የቃል አቀባዩ መግለጫ አመልክቷል።

በዓለም አቀፉ ወረርሽኞችን የማጥፋት ትብብሮች ግንባር ቀደም ሚና መጫወቷን እንደምትቀጥልም አመልክተዋል። የቃል አቀባዩ መግለጫ በዶክተር ቴዎድሮስ ላይ የማስፈራራት ዛቻ ጭምር አድርገዋል ተብለው በተጠቀሱት የታይዋን ባለሥልጣናትን በተመለከተም የተናገሩት ነገር ነበራቸው። ይህም፤ የታይዋን ዲሞክራቲክ ፕሮግሬሲቭ ፓርቲ ባለሥልጣናት ጉዳዩን ፖለቲካዊ መልክ እንዲይዝ ለማድረግ ከመሻታቸው ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።

የታይዋኑ ፓርቲ ባለሥልጣናት የተከሰተውን ወረርሽኝ ተመርኩዘው ከቻይና መገንጠል መኾኑንም በግልጽ እንዲህ ያለው ሁኔታ በፍጹም ሊሳካ የማይችል ነው። አንቶኒዮ ጉቲሬዝ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዓለም ጤና ድርጅት ላይ የሰነዘሩት ወቀሳ ወቅቱን ያልጠበቀ ብለውታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዓለም ጤና ድርጅት ላይ ያቀረቡት ወቀሳ ወቅቱን ያልጠበቀ ነው ሲሉ እንዳጣጣሉት ሁሉ፤ ጠንከር ባለ አቋም ሰሞናዊውን ዘመቻ በማውገዝ ቀድሞ ድምፁን ያሰማው የአፍሪካ ሕብረት ነበር። የሕብረቱ ዋና ፀሐፊ ሙሳ ፋኪ ማህማት፤ አሜሪካ በዶክተር ቴዎድሮስ እና በዓለም ጤና ድርጅት ላይ የከፈተችው ዘመቻ እንዳስገረማቸው ገልጸው፤ የአፍሪካ ሕብረት ከዶ/ር ቴዎድሮስና ከዓለም ጤና ድርጅት ጎን መኾኑን አመልክተዋል።

ኮሮና ቫይረስን ለመዋጋት እየሠሩ ያሉትንም ሥራ አወድሰዋል። አሁን ኮሮናን ማጥፋት ላይ መረባረብ እንጂ ክሱ በኋላ ይደርሳልም ብለዋል። የአፍሪካውያን መሪዎችም በተመሳሳይ ከዶ/ር ቴዎድሮስ ጋራ መኾናቸውን በመግለጽ በኢንተርኔት የድጋፍ ፊርማ እየተሰበሰበም ነው። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ከዶክተር ቴዎድሮስ ጋር በስልክ የተገናኙት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ ከኮሮና ቫይረስ ወቅታዊ መረጃዎችን በመሥጠታቸውና የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የዓለም ጤና ድርጅት ስለሚያከናውነው ተግባር አመስግነው፤ ዶክተር ቴዎድሮስ አመራራቸው ወቅቱንና ኃላፊነታቸውን የሚመጥነው ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ አካል በኾነው የዓለም ጤና ድርጅት እንዲሁም ድርጅቱን በሚመሩት ሰዎች እና በሰዎች በሚቆጠሩት ሠራተኞቹ ላይ የሚሰነዘረውን ወቀሳና ዛቻ፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ነው ማለታቸውን የቻይና የመረጃ ምንጭ ዥንዋ ዘግቧል። (ኢዛ)

ስደተኞች እና እነጅቡቲ

በዘመነ ኮሮና ኢትዮጵያውያንን በግድ ጭምር ከአገራቸው በማስወጣት ጅቡቲ እና ሳውዲ ዐረቢያን የሚስተካከላቸው የለም። ጅቡቲ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ወዲህ ሕገወጥ ናቸው በሚል ያባረረቻቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሦስት ሺሕ በላይ ደርሷል። ያልተጠበቀ ነው በተባለው የጅቡቲ እርምጃ የተባረሩት ኢትዮጵያውያን ዜጐች ማረፊያቸውን ያደረጉት ድሬዳዋን ነው። በድሬዳዋ በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ተደርጓል።

ሳውዲ ዐረቢያም በተመሳሳይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እያደረገች መኾኑ አነጋጋሪ የነበረ ዜና ነው። በተለይ የሳውዲ ዐረቢያ በዚህ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከአገራዊ ለማስወጣት እየወሰደች ያለችው እርምጃ፤ በኢትዮጵያ ወገን ሳያሳስብ አልቀረም። (ኢዛ)

በኮሮና ቫይረስ የሞተ ሰው አስክሬን እንዳይገባ የተሠጠው ውሳኔና አስቸኳይ አዋጁ

በኮሮና ቫይረስ የሞተ ሰው አስከሬኑ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓጓዝ ወይም እንዳይመጣ ይደረግ ዘንድ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ ይህንን ያስታወቀው በኮሮና ቫይረስ የሞተ ሰው አስክሬን በሚነካካበት ወቅት በሽታው ወደ ሌላ ሊተላለፍ የሚችል በመኾኑ ነው።

ከዚህ ሥጋት አንፃር ኢንስቲትዩቱ ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን በጻፈው ደብዳቤ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ አየር መንገዶች በኮሮና ቫይረስ የሞተ ሰው አስክሬን ይዘው እንዳይመጡ ይደረግ ብሏል። በመኾኑም ሲቪል አቪየሽን ወደ ኢትዮጵያ በረራ የሚያደርጉ የሁሉም አየር መንገዶች ኮሮና ቫይረስ የሞተ ሰው አስክሬን ይዘው እንዳይመጡ እንዲያሳስብለት ጠይቋል።

ከየትኛውም አገር ወደ ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የሞተ ሰው አስክሬን እንዳይገባ የሚለውን ማሳሰቢያ ተከትሎም ሲቪል አቪየሽን ይህንኑ ማሳወቁ ታውቋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ መንግሥት ባወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የሚሞት ሰው ቀብር በመንግሥት ሊፈጸም የሚችል መኾኑን አሳውቋል። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና እስከ 200 ቢሊዮን ብር የሚገመተው ኪሣራ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በእጅጉ እንደሚደቁስ የታወቀው ቀድሞ ነው ማለት ይቻላል። ኢኮኖሚያዊ ቀውሱ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም መኾኑ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የአፍሪካ አገሮች ላይ ግን አስከፊ እንደሚኾን እየተገለጸ ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይህንኑ የሚያመላክቱ ናቸው።

ነገሩን የበለጠ አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ የአፍሪካ አገሮች የዚህን ወረርሽኝ ሊያስከትልባቸው የሚችለውን ጉዳት ቀንሰው ወይም አነስተኛ በኾነ ጉዳት ቢሻገሩት እንኳን፤ ኢኮኖሚያቸውን መልሰው ወደ መስመር ለማስገባት እንዲህ ቀላል እንደማይኾንላቸው ከወዲሁ መተንበዩ ነው። አሁን ከጅምሩ እየታየ ያለውም እውነት ይህ ነው።

ወትሮም የኮሳሳ ኢኮኖሚ መገለጫዎች በመኾን የሚጠቀሱት የአፍሪካ አገሮች፤ ይህ በኢኮኖሚ አንቱ የተባሉትን ኃያላን አገራት እያንበረከከና አሁንም መጨረሻቸውን ለማወቅ በተቸገሩበት እንደኾነ ይታወቃል። ከዚህ ወረርሽኝ ጥፋት አንፃር ሲታይ አፍሪካውያን በየትኛው ትከሻቸው ይቋቋሙታል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የግድ የኢኮኖሚ ባለሙያ ትንታኔ የሚያስፈልገው አይደለም። ከሰሞኑ የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርቱ “የአፍሪካ ኢኮኖሚ ከ3.8 በመቶ የሚወርድ መኾኑ አንዱ ነው” ይህ ማለት የኢኮኖሚ እድገቱ 1.8 በመቶ ብቻ ሊኾን የሚችል ሲሆን፣ ይህ በየአገሮቹ አንፃር ሲታይ ዜሮ ሊኾን የሚችሉ አገሮች ሊኖሩ የሚችሉ መኾኑን ያሳያል።

በቅርብ እየተከታተልን ባለነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንፃር ደግሞ፤ ችግሩ ምን ያህል የከፋ መኾኑን ለማሳወቅ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ብቻ በምሳሌነት ማንሳቱ አንድ ማሳያ ይኾናል። አራት ወር ባልሞላ ጊዜ 550 ሚሊዮን ዶላር አጥቷል። እንደ ኢትዮጵያ ያለ ደሃ አገር መንፈቅ ባልሞላ ጊዜ ከአንድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭዋ ከኾነው አየር መንገድ ይህንን ያህል ገቢ ማጣት አስከፊ የሚባል ጥቃት ነው።

በኢትዮጵያ ለአገሪቱ በዚህን ያህል ደረጃ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያስገኝ አንድም ተቋም የሌላት ከመኾኑ አንፃር፤ ኮሮና ይዞት የመጣው ጣጣ የአገሪቱን ግዙፍ ኩባንያ በማንበርከክ ላይ መኾኑን አሳይቷል። ገናና ስም ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰፊ የገበያ ሽፋኑ እና የቢዝነስ ግኝት ሲታይም በአቪየሽን ኢንዱስትሪ አፍሪካ እንዳጣችው ከሚገመተው 4.2 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ኢትዮጵያ በአየር መንገድዋ የአንበሳውን ድርሻ እንድትይዝ አድርጓታል።

ከዚህ ባሻገር የአገር ውስጥ ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል ሳይሆን በእጅጉ እየተመታ ነው። የወጪ ንግዱ ወርዷል። የገቢ ንግዱ ከዓለም አገሮች ቀውስ ጋር ተያይዞ እየተሰነካከለ ነው። ብዙ ኩባንያዎች ሠራተኞች ወደመቀነስ ለመግባት እያመለከቱ ቢኾንም፤ መንግሥት ይህንን እንዳያደርጉ በመከልከሉ፤ አሁን ባለው ደረጃ የሠራተኛ ቅነሳ አልተስተዋለም። ብዙ ኩባንያዎች ግን ሥራቸው እየታጎለ ነው። ባንኮች የብድሩን ብር ለመሰብሰብ ባለመቻላቸው ለተበዳሪዎቻቸው የብድር ወለድ ቅነሳና የብድር መክፈያ ጊዜ እያራዘሙ ነው። ይህ የንግዱን እንስቃሴ ኳራንቲን ውስጥ እየከተተው ከመኾኑም በላይ፤ በኢትዮጵያ የቢዝነስ ዘርፍ በአትራፊነታቸውና ከፍተኛ ዲቪደንድ በመክፈል የሚታወቁት ባንኮች፤ ዘንድሮ የለመዱትን ትርፍ ማግኘት እንደማይችሉ ከወዲሁ እየታየ ነው። የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ከተለያዩ የባንክ ባለሙያዎች የሰበሰበው መረጃም ይህንኑ ነው የሚያመለክተው። ከ25 ዓመታት በላይ ያለማቋረጥ የትርፍ ዕድገቱ እየጨመረ መጥቶ እዚህ የደረሰው የባንኮች ትርፍ እንደቀደመው ጊዜ አይኾንም። ምናልባት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ያገኙት ትርፍ መልካም ትርፍ የተገኘበት በመኾኑ ቀሪዎቹን ወራት ይደግፋል ተብሎ በመታመኑ እንጂ፤ አሁን ያለበት ደረጃ ኪሣራ ውስጥ ሊጨምራቸው ይችል እንደነበር ይጠቅሳሉ።

ስለዚህ አሁን ያለው አማራጭ ቢዝነሳቸው የተቀዛቀዘና የሞተባቸው ተበዳሪዎችን በተለያየ መንገድ ከመንግሥት ጋር በመኾን በመደገፍ ይህንን ጊዜ እንዲያልፉ ማድረግ ነው። ችግሩ ግን አሁን እንደሚታሰበው የወረርሽኙ ጣጣ በሁለትና በሦስት ወሮች ውስጥ ካልተቃለለ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የሚጠብቃቸው ኢኮኖሚያዊው ቀውስ የበረታ ይኾናል። በመኾኑም ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕርዳታ የሚያስፈልግ መኾኑንና መንግሥት መፍትሔ የሚኾኑ ተጨማሪ ውሳኔዎችን መወሰን የሚጠበቅበት መኾኑንም ያስረዳሉ። አሁን አንድ ተስፋ እየተደረገበት ያለው ነገር G20 የሚባሉት ባለጸጋ አገሮችና ሌሎች ለጋሾች ብድር ለማቅረብ ዕርዳታ ለመሥጠት መስማማታቸው ካልኾነ፤ ሌላው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ፈተናው የበዛ ይኾናል።

በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን ለባንኮች 15 ቢሊዮን ብር እንዲለቀቅ መደረጉና መንግሥት ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ከመንግሥት ግምጃ ቤት አምስት ቢሊዮን ብር እንዲመደብ ወስኗል። ኾኖም አሁን እየታየ ካለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አንፃር ምናልባትም በአገሪቱ እስከ ዛሬ ተወስነው የሚያውቁ ውሳኔዎችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሊደረጉ እንደሚችሉ እነዚሁ የባንክ ባለሙያዎች ሳይጠቀሙ አላለፉም። መንግሥትም በኢኮኖሚ ውስጥ የሚታየውን ሁኔታ በማየት ተጨማሪ ውሳኔዎችን ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ እንደተጠበቀ ኾኖ ስለዚህ ወረርሽኙን ለመከላከል እየተደረገ ካለው እንቅስቃሴ ጐን ለጐን ኢኮኖሚውን የቁልቁለት ጉዞ ፍጥነት የሚቀንሱ እርምጃዎች ደረጃ በደረጃ መወሰድ የግድ መኾኑ ነው። ይህንንም ለማድረግ መንግሥትና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ የንግድ ሕብረተሰቡ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር መረባረብ ይኖርባቸዋል።

የኮሮና ቫይረስ እያስከተለ ያለውን እና ከዚህም በኋላ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ ስለመኾኑ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ይፋ ያደረገው ጥናታዊ ሪፖርት አመላክቷል።

እንደ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር፤ የኮሮና ቫይረስ አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ከኾነ የኢትዮጵያ መንግሥት ከ44 ቢሊዮን ብር በላይ ሊያሳጣው እንደሚችል አመላክቷል። ይህ በሦስት ወር ብቻ ሊያጣ የሚችለው ሲሆን፤ ችግሩ ከሦስት ወራት በላይ የሚቀጥል ከኾነ መንግሥት እያጣ የሚሔደው ይጨምራል።

በጥናቱ ለአብነት እንዳስቀመጠውም የኮሮና ወረርሽኝ ችግር በስድስት ወራት ውስጥ ሊፈታ የማይችል ከኾነ፤ መንግሥት 139 ቢሊዮን ብር ኪሣራ ሊያጋጥመው እንደሚችል አመልክቷል።

ወረርሽኙን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስና ማኅበራዊ ጉዳት በቀጣይም የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያቀጭጨውና በአጭር ጊዜ የተጠናው ይኸው የማኅበሩ ጥናት ሳያመለክት አላለፈም።

ወረርሽኙን በቶሎ መቆጣጠር ካልተቻለም፤ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በአሥር በመቶ እንደሚቀንሰው የሚያመለክተው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጥናት፤ በዚህን ደረጃ ኢኮኖሚው ቀነሰ ማለት ደግሞ እንደ አገር ወደ 204 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ኪሣራ የሚያጋጥም መኾኑን ነው።

ጥናቱ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ብቻ ሳይሆን፤ እንዲህ ያለው ጉዳት እንዳይደርስ ወይም ለመቀነስ የሚቻልባቸው መንገዶች ሊኖሩ የሚችሉ መኾኑን አመላክቷል። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበሩም ኾነ ሌሎች የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከከፋ ጉዳት ለመዳን፤ እንዲሁም ኪሣራውን ለመቀነስ የመጀመሪያው እርምጃ ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ አበክሮ መሥራት ነው እያሉ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ መደገፍ ያለባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች በልዩ ትኩረት እገዛ እንዲደረግላቸው ማድረግ ነው። (ኢዛ)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች

ባሳለፍነው ሳምንት ትልቁ ፖለቲካዊ ውሳኔ ተደርጐ የሚወሰደው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁና ይህም አዋጅ በፖርላማ መጽደቁ ነው። ኢትዮጵያ ከፖለቲካ ጉዳዮች ባሻገር ከጤና ጋር ተያያዘ የታወጀ የመጀመሪያው አስቸኳይ አዋጅ ኾኖ ሊጠቀስ የሚችልም ኾኗል።

አዋጁ ክልከላዎችንና ምን ሲደረግ ነው እርምጃ የሚወሰደው የሚለውን ጥያቄ አዋጁ በታወጀበት ቀን የሚመለስ ባለመኾኑ፤ ከዚህ ቀደም ከነበሩ አዋጆች በተለየ ሲታይ ሰንብቶ ነበር። ኾኖም የትኞቹ ይከለከላሉ፣ የትኞቹ መብቶች ይበደላሉ የሚለውና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ቀድመው ባለመጠቀሳቸው ብዥታ ፈጥሮም ነበር። እንዲህ የኾነበትና ዝርዝር ጉዳዮችን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚያወጣ መኾኑ የተፈለገበት ምክንያት በሰፊው ተብራርቷል። ይህ ከኾነ በኋላ ግን ቅዳሜ ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዝርዝር የማስፈፀሚያ ደንብ ይፋ በማድረግ ብዥታውን እንዲገፈፍ አድርጓል።

የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንብን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ይፋ ባደረጉበት ማብራሪያቸው፤ ማስፈፀሚያ ደንቡ አጠቃላይ አራት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት መኾኑን ገልጸዋል። ይሄውም ክልከላን የሚያስቀምጥ፣ ግዴታዎችን የሚጥል፣ የአስፈፃሚ አካላትን ክንውን እንዲሁም ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ መኾኑን ጠቅሰው፤ ክልከላን በሚመለከተው ክፍል ማንኛውም ሃይማኖታዊ ይሁን ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ እድር፣ ደቦ፣ እቁብና ሌሎችም ከአራት ሰው በላይ ስብሰባዎች ክልክል መኾናቸውን የሚያመለክት ነው። አራት ሰዎችም ቢኾኑ ሁለት የአዋቂ ሰው እርምጃ የጠበቀ መኾን እንዳለበት ዓቃቤ ሕጓ ማብራሪያ ያስረዳል።

ቀብርና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ሲኖሩ ግን እየታዩ ሊፈቀዱ የሚችሉበት አሠራር መኖሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጓ፤ በኮሮና ቫይረስ የሚሞት ሰው የቀብር ሥርዓት የመንግሥት ጉዳይ መኾኑን አመልክተዋል። ኾኖም ቤተሰብ እንዴት ሊቀብር ይችላል የሚለው ላይ ተጨማሪ መረጃ ሊሠጥበትና ሊታይ የሚችል መኾኑን ግን ጠቁመዋል።

ታራሚዎች ከጠበቆቻቸው ጋር አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲገናኙ የሚፈቀድ ቢሆንም፤ ጥየቃ ለሚሔዱ ሰዎች የማይፈቀድ መኾኑ በዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልከላ ክፍል ተቀምጧል።

በፖሊስ የተያዙ እስረኞችንም ስንቅ ከማቀበል በስተቀር መገናኘት የተከለከለ መኾኑንም ለማወቅ ተችሏል። ሌላው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጠው ክልከላ በድንበር አካባቢ ከካርጎ፣ የደረቅና ፈሳሽ ጭነት አገልግሎቶች በስተቀር ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዝግ መደረጋቸው ነው።

የቤት ተከራዮች በራሳቸው ፍላጎት ካልወጡ በስተቀር ማስወጣትና ኪራይም መጨመር፤ እንዲሁም ሠራተኞችን መቀነስና የሥራ ቅጥር ውል ማቋረጥ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተከልክሏል።

በዚህ ደንበ መሠረት ተማሪዎችና መምህራን በኦን ላይን ካልኾነ በአካል እንዲገናኙ የማይፈቀድ ሲሆን፤ ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ የሕፃናትም ይሁን ለሌሎች መጫወቻ ስፍራዎች እንዲሁም የእጅ መጨባበጥ ሰላምታ የተከለከለ ነው።

በትራንስፖርት ዘርፍም አገር አቋራጭ ካለው ወንበር ከ50 በመቶ በላይ ተሳፋሪ መጫን የተከለከለ ሲሆን፤ የኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡርም የመጫን አቅሙን በ50 በመቶ በመገደብ እንዲሠራ ተደንግጓል። በእንቅስቃሴ ወቅት ሰዎች የአፍ ማስክ (መሸፈኛ) ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ወይም እንደመሃረብ፣ ስካርቭ ያሉ የአፍ መሸፈኛ ማድረግ ይቻላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለ15 ቀን ተግባራዊ የሚደረግ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ የነበረው የትግራይ ክልል ምክር ቤት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሦስት ወሮች እንዲራዘም የወሰነውም በዚህ ሳምንት ነበር።

ምክር ቤቱ ሚያዝያ 1 ቀን ባካሔደው አስቸኳይ ጉባኤ በተለያዩ አገሮች የቫይረሱ ሥርጭት በፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱና አስጊ ደረጃ ላይ በመኾኑ፤ በሽታውን ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ የሚኾንበትን ጊዜ ወደ ሦስት ወር እንዲራዘም ወስኗል።

ይህም ውሳኔ ከመጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ታሳቢ ተደርጐ የሚቀጥል ይኾናል። ከዚሁ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚ የሚደረጉ ድንጋጌዎች ላይ በመነጋገርም እንዲተገበሩ ውሳኔ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ ውሳኔ ግን ከፌዴራል መንግሥቱ አዋጅ ጋር እንዳይጋጭ የሚል ሥጋት መፍጠሩ አልቀረም። በተለይ ማንኛውም ወደ ትግራይ ክልል የሚገባ ሰው በራሱ ወጪ ለ14 ቀን ኳራንቲን ይቀመጣል የሚለው ድንጋጌ፤ ክልሉን ይጎዳል የሚለው አንድ አስተያየት ሲሆን፤ በተለይ ሸቀጦችና ሌሎች ምርቶች እንዳይገቡና እንዳይወጡ በማድረግ ችግር ይፈጥራል የሚል አስተያየት እየተሰነዘረ ነው። ሌላው የፌዴራል መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሁሉም ክልሎች ተፈፃሚ የሚኾን እና ይህንንም የሚፃረር ሌላ ሕግ ተግባራዊ እንደማይኾንም ተገልጿል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፌዴራል መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአስገዳጅነቱ የሚፈጸሙ ሕግጋቱን አውጥቷል። (ኢዛ)

ተሳፋሪ በግማሽ፤ ዋጋ በእጥፍ

ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የታክሲ ትራንስፖርት ታሪፍ ማስተካከያ ማድረጉ ሌላው ዜና ነበር። በተስተካከለው ታሪፍ መሠረት ዝቅተኛው የታክሲ ዋጋ ሦስት ብር ሲሆን፤ ከፍተኛው ደግሞ 12 ብር ከ50 ሣንቲም እንዲኾን ተወስኗል። ከዚህ ቀደም አጭር የጉዞ ታሪፍ 1.50 ሣንቲም እንደነበር ይታወሳል።

በመመሪያው መሠረት ታክሲዎች ከመጫን አቅማቸው 50 በመቶ ብቻ እንዲጭኑ የሚገደዱ በመኾኑ፤ ታሪፉም በዚያው ልክ እጥፍ እንዲኾን በመደረጉ ነው። በዚህም መሠረት ታክሲዎች አዲሱን ታሪፍ የሚያስከፍሉት የመጫን አቅማቸውን በግማሽ ቀንሰው ተሳፋሪዎችን በመያዝ ነው። የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ታስቦ የወጣ መመሪያ ነው።

ይህንን መመሪያ ተላልፎ የተገኘ አሽከርካሪ የአምስት ሺሕ ብር ቅጣት የሚጠብቀው ሲሆን፤ በወንጀልም ተጠያቂ እንደሚኾን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

ለዚህም በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ሕገ ወጥ ተግባራት ሲያጋጥሙ ጥቆማ የሚሠጥበት የጥሪ ማዕከል መዘጋጀቱንም ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም በታክሲ አገልግሎት የሚያጋጥሙ ሕገወጥ ተግባራትን ተከታትለው እርምጃ የሚወስዱ ከ100 ያላነሱ ሞተር ሳይክሎች መሰማራታቸውን መረጃው ያመላክታል። (ኢዛ)

በአዲስ አበባ የታሰበው የቤት ለቤት ምርመራ

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች ጐን ለጐን የምርመራ ሽፋኑን ከፍ የማድረግ ሥራ አስፈላጊ መኾኑ ታምኗል። ከዚህ አንፃር የአዲስ አበባ አስተዳደር ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በተመረጡ የከተማው ወረዳዎች ምርመራ የሚጀምር መኾኑን አሳውቋል። ምርመራው ተጋላጭ ሊኾኑ ይችላሉ ተብለው ከተለዩ ወረዳዎች የሚጀምር መኾኑንም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገልጸው፤ በመዲናዋ 117ቱም ወረዳዎች ተግባራዊ ይኾናል።

እንዲህ ያለውን የምርመራ ሒደት ለማከናወን ጡረታ ላይ የነበሩና በሞያው ልምድ ያላቸው ከ1 ሺሕ 200 በላይ ሐኪሞች ካሉት የሐኪሞች ቡድን ጋር የሚሠራ ይኾናል።

ከቤት ለቤት ምርመራው በተጨማሪ በሚቀጥለው ሳምንት ተማሪዎች በያሉበት ኾነው ትምህርት እንደሚጀምሩና የምዝገባ መርሃ ግብሩም እንደሚቀጥል ከንቲባው ተናግረዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ