Ethiopia Zare's weekly news digest, week 32nd, 2012 Ethiopian calendar

ከሚያዝያ 5 - 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሠላሳ ሁለተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከሚያዝያ 5 - 11 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ያሳለፍነው ሳምንት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ የኾነው የትንሣኤ በዓል የሚከበርበት የመጨረሻ ሳምንት የዋለበት ነው። በቀጣይ ሳምንት ደግሞ የታላቁ ረመዳን ጾም ይጀምራል። እነዚህ የሃይማኖት ተከታዮች በሕብረት ኾነው የሚያከብሩት ቢኾንም ዘንድሮ እንደቀደመው ጊዜ የሚከበሩ አይኾኑም። ከሰሞኑ የትንሣኤ በዓል ዋዜማ ላይ የተመለከትነው ይህንኑ ነው።

ለወትሮው በዓሉ መዳረሻ የመጨረሻ ሳምንት ላይ ይታይ የነበረው የበዓል ድባብ ዘንድሮ እምብዛም አልታየም። በቤተክርስቲያኖች ደምቀው ይታዩ የነበሩ የሃይማኖታዊ ክዋኔዎች በቤት ውስጥ እንዲወሰኑ ኾኗል። ጥቂት የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን እየመሩ ክዋኔው በቴሌቪዥን የተላለፈበት የትንሣኤ በዓል ቢኖር ዘንድሮ ብቻ ነው።

ይህ ያሳለፍነውን ሳምንት በተለየ እንድንመለከተው ያደረገ ሲሆን፤ ሌሎች ከበዓሉ ጋር የሚገናኙ እንቅስቃሴዎችና ክንውኖችም በተመሳሳይ የወትሮው ገጽታን ድባብ አልታየባቸውም። ይህ ሁሉ የነበረው ዓለምን እየደቆሳት ባለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ነው።

ያሳለፍነው ሳምንት ሌላው ገጽታ ከዚሁ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ መንግሥት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የወጣው ዝርዝር መመሪያ በተግባር የጀመረበት ነው። የግል ተሽከርካሪዎች በፈረቃ እንዲሽከረከሩ መመሪያ መውጣቱ አንዱ ነው። ከሰኞ ሚያዝያ 12 ቀን 2012 ጀምሮ ተግባራዊ ይኾናል።

የበዓሉ ድባብ የተቀዛቀዘ ቢሆንም፤ ዜጐቹ በዓሉን ተጠንቅቀው እንዲያከብሩ፤ በዓሉን ለማክበር አቅም የሌላቸውን ደግሞ ብዙዎች እጃቸውን ሲዘረጉ የታየበት ነበር። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ፣ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴና ከንቲባ ታከለ ኡማ የአንዳንድ ድሆች መኖሪያዎችን በማንኳኳት የበዓል ስጦታ ያበረከቱበት የትንሣኤ በዓል ነበር።

እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ሚያዝያ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 105 መድረሱ ሪፖርት የተደረገበት ሳምንት ነው። እንደ ጤና ሚኒስቴር መረጃ በዚህ ሳምንት ሪፖርት የተደረጉት የቫይረሱ ተጠቂዎች ካለፉት አምስት ሳምንታት ከተመዘገቡት ሁሉ ብልጫ ያሳየ ነው። በአንድ ቀን ከ800 በላይ ሰዎችን መመርመር የተቻለበት ቀን ቢኖር ይህ ሳምንት መኾኑ የተሰማበት ነው። በሳምንቱ ውስጥ ሌላው አነጋጋሪ የኾነው ጉዳይ በአሜሪካና በዓለም ጤና ድርጅት መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ከርሮ፤ አሜሪካ ለጤና ድርጅቱ የምትሠጠውን የገንዘብ ድጋፍ ማቆሟን መግለጿ ነው። ይህ ውሳኔዋ ተቃውሞ ያስነሳ ኾኗል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዓለም ጤና ድርጅት በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ባሳየው እንቅስቃሴ ደስተኛ ያለመኗን የሚያመለክት መግለጫ በመሥጠት ጃፓን የራሷን ሐሳብ ሰንዝራለች። ቅሬታ ቢኖራትም ለድርጅቱ የምታዋጣውን ገንዘብ አልከለክልም ብላለች። ይሁንና በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ድርጅቱ መገምገም አለበት ብላለች።

ብዙዎቹ የዓለምም ኾነ የአገር ውስጥ ዜናዎች አሁንም በዓለም አቀፍ ደረጃ እየሰፋ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጉዳይ ነው። የአገር ውስጥ መረጃው እንደሚጠቁመን እስካሁን በኢትዮጵያ በቫይረሱ የሞተው ሦስት ሰው ብቻ ነው። ሦስት ኢትዮያውያንን በዚህ ቫይረስ ያጣችው ኢትዮጵያ፤ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ላይ ግን ያደረሰው ጉዳት አስደንጋጭ ስለመኾኑ በይበልጥ የሰማንበት ሳምንት ኾኗል። ይህም በአሜሪካ ብቻ ከኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲዎች የተሰባሰበው መረጃ 100 የሚኾኑ ኢትዮጵያውያን በዚህ ቫይረስ መሞታቸው ነው። ይህ የሳምንቱ አስደንጋጭ ዜና ነበር። ቁጥሩ ከዚህም በላይ እንደሚኾን የተገመተ ሲሆን፤ አሁን በቫይረሱ ተጠቂ ሊኾኑ በሚችሉበት አካባቢ ውስጥ መኾናቸው እየተነገረ ነው።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እያስከተለ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጥቃት ጐልቶ የታየ ሲሆን፤ የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ እንቅስቃሴያቸው መስተጓጐሉን እያመለከቱ ነው። የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ሰሞኑን እንደገለጸው ዕለታዊ የገንዘብ እንቅስቃሴው በግማሽ መቀነሱን ነው። ፋይናንስ ተቋማት ወረርሽኙን ለመከላከል የተለያዩ ውሳኔዎች እያሳለፉ ሲሆን፤ በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕድለኞች ለባንኩ የሚከፍሉትን ወርሃዊ ክፍያቸውን ለሦስት ወር እንዳይከፍሉ መወሰኑ ይጠቀሳል። በሦስት ወር ውስጥ ከእነዚህ ደንበኞቹ መሰብሰብ የነበረበትን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ከሦስት ወር በኋላ ትከፍሉኛላችሁ ብሏል።

በዚህ ሳምንት ከተሰሙ ወሬዎች በምሥራቅ አፍሪካ ቁጥሩ የበዛ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን ያስቆጠረችው ጅቡቲ ለኢትዮጵያ አንድ ውለታ ውላለች። ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ለምትልካቸው ምርቶች በወደብ ታስከፍል የነበረውን ክፍያ 82 በመቶ ለመቀነስ መስማማቷ ነው።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በመድን ሽፋን ሰንጠረዥ ውስጥ የለም። የዋስትና ሽፋኑ አይታወቅም። ይሁንና ኒያላ ኢንሹራንስ ቫይረሱ ለሚያስከትለው ጉዳት የመድን ሽፋን መሥጠት መጀመሩን ያሳወቀው በዚህ ሳምንት ነው። በእነዚህ በለሎች ሳምንታዊ ክዋኔዎች የተወሰኑትን የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት እነሆ! ይላል።

ከሥጋት ጋር የተከበረው ፋሲካ

የዘንድሮ ትንሣኤ የወትሮውን ድባብ አይታይበትም። በዋዜማው የተለመደው የግብይት ሥርዓትም በሥጋት የተሸበበና ቀዝቃዛ ነበር። ሁሉም በሥጋት የተወጠረበት፣ በዓሉን ለማክበር የተቀዛቀዘ ስሜት የታየበት ነው። በተወሰነ ደረጃ በዓሉን ለማክበር የታዩት እንቅስቃሴዎችም ቢሆኑ፤ ከዚህ ቀደም ከሚታየው የተለየ በተደበላለቀ ስሜት የሚከወኑ ኾነዋል።

እንደ ትንሣኤ ያሉ በዓላት በዋዜማቸው አብዝተው ይደመጡ የነበሩ በዓል ቀመስ ዜማዎችም ቢሆኑ፤ በቀደመው ልክ ያልተሰማበት፣ በምትካቸው ስለኮሮና ቫይረስ የተሠሩ አዳዲስ ዜማዎች ጐልተው የሚሰሙበት አውድ ዓመት ሳምንት እያለፈ ነው። “ጤና ለሠጠው ሰው ዕድሜውን ላደለው …” የሚለው በአውድ ዓመት ማድመቂያነት የሚታወቀውን ዘፈን ደጋግመው ያስተጋቡ የነበሩ ሚዲያዎች፤ ዛሬ ይህንን ዜማ ሸሽገዋል ወይም የሚያሰሙት በጨረፍታ ነው ማለት ይቻላል። ዘፈን ዛሬ የለም። በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከጸሎተ ሐሙስ ጀምሮ በየቤተክርስቲያኖቹ ይፈጸሙ የነበሩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎችን ለመመልከት ያልተቻለበት እና ስግደቱም በቤት ውስጥ እንዲካሔድ የተደረገበት ኾኗል። እኚያ በምዕመናን ተሞልተው ይሰገድባቸው የነበሩ ቤተክርስቲያኖች፤ የቀድሞ ድባባቸው ዘንድሮ የለም። የዘንድሮ የትንሣኤ በዓል በመንግሥትና በሃይማኖት ተቋማት ውሳኔ ሳምንቱን በሙሉ ሃይማኖታዊ ክንውኖች በቀጥታ የቴሌቪዥን መካሔዳቸውም የዘንድሮ የተለየ ነው። በተለያዩ ኩባንያዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያጨናንቃቸው የነበሩ ሚዲያዎች በዘንድሮው የትንሣኤ ዋዜማ ግን እንዲህ ያሉ መልእክቶችን የተቆጠቡበት ኾኗል። የሕትመት ሚዲያዎችም ወትሮ በዓል በደረሰ ቁጥር በኩባንያዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቶች ያብጥ የነበረው ገጾቻቸው ኮስሰው የታዩበት አውድ ዓመት ይኸው የዘንድሮ የትንሣኤ በዓል ነው። በየአውድ ዓመቱ በየአካባቢው ይታዩ የነበሩ የባዛር ዝግጅቶች ዘንድሮ ብርቅ ኾነዋል። በዓሉን አስታከው የሚዘጋጁ የሙዚቃ ድግሶች ዘንድሮ የሉም። ማስታወቂያዎቻቸውም አልተሰሙም።

በተለይ ለሁለት፣ ሦስት ሳምንት 20 እና 30 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጐባቸው በሚሊኒየም አዳራሽና በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሔዱት እና በየዕለቱ መቶ ሺሕ ጐብኝዎችን ያስተናግዱ የነበሩ የትንሣኤ ባዛሮች ሳይካሔዱ ቀርተዋል። ለዚህም ሲባል የወጣው ወጩ ውኃ በልቶታል። የሞቀ ገበያ ይካሔድበት የነበረው የሚሊኒየም አዳራሽ፤ ዛሬ ለኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ማከሚያ ይሁን ተብሏል። ሌሎች የገበያ ስፍራዎችም ቢሆኑ የወትሮ ድባብ የላቸውም። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የታየው ግብይትም ቀዝቃዛ ነው።

በአንፃሩ ደግሞ እስከሳምንቱ አጋማሽ ቀዝቀዝ ብለው የታዩ የገበያ ስፍራዎች ከሐሙስ ጀምሮ ግን ሳይታሰብ ሞቅ ብለው መታየታቸው ግራ የሚያጋባ ነበር። ለቫይረሱ ተጋላጭ በማያደርግ ሁኔታ ግብይት ይፈጸም የተባለው መመሪያ ተጥሶ፤ ለበዓሉ ግብአት የሚኾኑ ምርቶች የሚሸጡባቸው ቦታዎች በሰዎች ተጨናንቀው ታይተዋል። የከብት ገበያው ደርቶ ታይቷል። በቀዘቀዘ ገበያ የተጀመረው ሳምንት የበዓሉ ዋዜማ የመጨረሻ ቀናት ላይ ሰዎች እንቅስቃሴ አስፈሪ ነው ሊባል የሚችል ነበር። ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ በኾነ ሁኔታ የሚካሔደው የከብት እና የሌሎች ግብይቶች ደግሞ ሥጋት መኾናቸው አልቀረም።

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ግን የከብት ገበያ መጦፉ ደግሞ አደጋ አለው። አውድ ዓመት ነውና ጥሬ ሥጋ ለመብላት የናፈቀ ሁሉ ዘንድሮ ለዚህ አምሮት የሚኾን ስሜት ብዙም የለም። የሕክምና ባለሙያዎችም ጥሬ ሥጋ ከመብላት መቆጠብ ይኖርባችኋል በማለት ለሕብረተሰቡ ባስተላለፉት መልእክት፤ የዘንድሮ በዓል የተጠበሰ እንጂ ጥሬ ሥጋ ለመብላት የተመቸ አልነበረም። የሕክምና ባለሙያዎች ጥሬ ሥጋ መመገብ በዚህ ሰዓት መልካም ያለመኾኑን የሚመክሩት፤ ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ስለማይታወቅ፤ ሁሉም መጠንቀቅ ስለሚኖርበት ጥሬ ሥጋን በዚህ በዓል ወቅት መመገብ ፈጽሞ ተገቢ አይደለም በማለት ነበር። (ኢዛ)

በጎ ተግባራት

የበዓሉ ድባብ ቀዝቃዛ ቢሆንም፤ ዜጐች በበጐ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ድሆችን መልካም በዓል ያሉበት ሳምንት ነው። እንዲህ ያለው በጐ ተግባር በርከት ብሎ ታይቷል። በባለሀብቶች በወጣቶችና በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይህ ታይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውም የምግብ አቅርቦቶችን ለአዲስ አበባ አስተዳደር መለገሳቸው አንዱ ነው።

እያንዳንዱ ቤተሰብ ከሌላቸው ጋር “ማዕድ እንዲጋራ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት፣ በራሳቸው በኩል ለመስተዳድር የምግብ አቅርቦቶችን አስረክበዋል። ያስረከቡት የደረቅ ምግብ ዐይነት የከተማ መስተዳድሩ “እጅግ ተጋላጭ እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች” ብሎ ለለያቸው፣ ብዙ የቤተሰብ አባል ላሏቸው 1,000 ቤተሰቦች የሚበቃ እንደኾነም ተጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላው ክዋኔ ደግሞ የፋሲካ በዓልን አስመልክቶ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎችን ቦታው ድረስ በመገኘት ማበረታታቸው ነው። ከቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር በመኾን በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የተገኙት መሪዎቹ በተቋሙ እያገለገሉ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎችም የተለያዩ ስጦታዎችን ሠጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድና ኢንጅነር ታከለ ኡማ በተለያዩ ድሆች ቤት በመሔድ የበዓል ስጦታ ሠጥተዋል። በተመሳሳይ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴና ታከለ ኡማ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ላሉዋቸው አቅመ ደካሞች የበዓል ስጦታ አበርክተዋል። በቅርቡ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ድጋፍ ለሠጡ ወጣቶች ደግሞ፤ ኢንጅነር ታከለ 40 ከብት በማበርከት በየአካባቢያቸው ላሉ ድሆች እንዲያከፋፍሉ አድርገዋል። (ኢዛ)

ፋሲካና ጥሬ ሥጋ

ሥጋ ቤቶች ያልበሰለ ሥጋ እንዳያቀርቡ ተከልክሏል። ከፋሲካ በዓል ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሥጋ ቤቶች ጥብቅ ማሳሰቢያ ሠጥቷል። ጥብቅ ማሳሰቢያው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል በፌዴራል ደረጃ የወጣውን አዋጅ ተከትሎ የወጣ ሲሆን፤ ሥጋ ቤቶች ሊፈጽሙት ይገባል ብሎ ያወጣው ማሳሰቢያ ነው።

በአስተዳደሩ ማሳሰቢያ መሠረት ሥጋ ቤቶች በአስገዳጅነት ሊፈጽሙ ይገባል ብሎ ያስቀመጣቸው ስምንት ነጥቦች ሲሆኑ፤ ከምግብ ቤት ጋር የተያያዙ ሥጋ ቤቶች ጥሬ ሥጋ ለምግብነት እንዳያቀርቡም አግዷል። አስተዳደሩ በአስገዳጅነት ያስቀመጣቸው ስምንቱ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።

1. ማንኛውም ሥጋ ቤት (ሉካንዳ) ሥጋ አስገብቶ ከመሸጡ (አገልግሎት ላይ እንዲውል) ከመደረጉ በፊት ሙሉ ለሙሉ ሥጋ ቤቱንና መጠቀሚያ ቁሳቁሶችን በውኃ ሳሙናና በረኪና በመጠቀም ማጽዳት አለበት።

2. ማንኛውም ሥጋ ቤት (ሉካንዳ) የሚያስገባው ሥጋ ሕጋዊ እና ከታወቀ ቄራ ታርዶ የቀረበ መኾን አለበት።

3. ማንኛውም በሥጋ ቤት (በሉካንዳ) የሚሠራ ሠራተኛ የሥጋ ሽያጭ በሚያከናውንበት ጊዜ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ)፣ ቆብ፣ ጋዋን መጠቀም አለበት፣

4. በማንኛውም በሥጋ ቤት (በሉካንዳ) ገንዘብ የሚቀበልና ሥጋ የሚቆርጥ ሠራተኛ መለየት አለበት፣

5. በማንኛውም ሥጋ ቤት (ሉካንዳ) ውስጥ ለሠራተኞች የእጅ ሳሙናና ውኃ ተዘጋጅቶ በየጊዜው እጃቸውን በመታጠብ አገልግሎት መሥጠት አለባቸው፣

6. በማንኛውም ሥጋ ቤት (ሉካንዳ) ሽያጭ በሚከናወንበት ወቅት ተገልጋዮች ከመሸጫ መስኮቱ 1 (አንድ) ሜትር ርቀው እንዲቆሙና እንዲገለገሉ መደረግ አለበት።

7. በማንኛውም ሥጋ ቤት (ሉካንዳ) ድርዙደት ውስጥ የተገልጋይ ቁጥር ከሁለት በላይ በሚኾንበት ወቅት ድርጅቱ ተገልጋዮችን እያንዳንዳቸው ርቀታቸውን በየሁለት እርምጃ ጠብቀው እንዲቆሙና እንዲገለገሉ መደረግ አለበት፣

8. ከምግብ ቤቶች ጋር የተያያዙ ሉካንዳ ቤቶች ውስጥ ያልበሰለ ሥጋ (ቁርጥ/ጥሬ ሥጋ፣ ያልበሰለ ክትፎ) ለምግብነት ማቅረብ ለበሽታው ስለሚያጋልጥ የተከለከለ ነው። (ኢዛ)

ኮሮናና ኢትዮ ቴሌኮም ቅናሽ

ከለውጡ ወዲህ በተለያዩ አገልግሎቶቹ ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ ሲጓዝ የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም የኮሮና ወረርሽኝም እንደገና የአገልግሎት ማሻሻያ እያደረገ እና ደንበኞቹን ለመድረስ ምክንያት ኾኖታል። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ኢትዮ ቴሌኮም እንዳስታወቀው፤ ኢትዮ ቴሌኮም “በቤትዎ ይቆዩ” የሚል ቅናሽ የተደረገበት ዕለታዊ የጥቅል አገልግሎት ይፋ ማድረጉን አስታውቆ፤ ይህም ተገልጋዮች በቅናሽ ዋጋ እንዲጠቀሙ ያስችላል ተብሏል።

ሕብረተሰቡ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ብዙው ሰው በቤቱ በመቀመጡ፤ በተለይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን የሚገልጸው የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ፤ ይህንኑ ተከትሎ የአገልግሎት ቅናሽ እንዲየደርግ ሲቀርብለት የነበረውን ጥያቄ በማጤን አወንታዊ ምላሽ መሥጠቱ ታውቋል። በዚህም መሠረት የተሻለውን የኢትዮ ቴሌኮም ትራፊክ ከግምት ውስጥ በማስገባት የጥቅል አገልግሎት ማሻሻያ ቅናሽ መደረጉን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ አስታውቀዋል።

በተለይ ጠዋት 12 ሰዓት እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ድረስ ያለው ትራፊክ መጨናነቁ ሻል ያለ በመኾኑ፤ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የአገልግሎት ቅናሹ ተደርጓል። በዚህ የሰዓት ገደብ ውስጥ እንዲፈጸም ተወስኗል።

“በቤትዎ ይቆዩ” የጥቅል አገልግሎት የቅናሽ ማሻሻያ የተደረገባቸው ዕለታዊ አገልግሎቶችን በተመለከተም፤ በ5 ብር 30 ደቂቃ የድምፅና 20 አጭር መልእክት፤ ይህም ከቀድሞው አንፃር የ53 በመቶ ቅናሽ ያሳያል፣ በ5 ብር 100 ሜጋ ባይት፣ የኢንተርኔት ዳታና 20 አጭር መልእክት ወይም በ10 ብር 250 ሜጋ ባይት፣ የኢንትርኔት ዳታና 20 አጭር መልእክት ወይም በ10 ብር 250 ሜጋ ባይት የኢንተርኔት ዳታና 20 የአጭር የጽሑፍ መልእክት - ይህም ከቀድሞ አንፃር የ56 በመቶ ቅናሽ አለው። በ15 ብር ደግሞ 30 ደቂቃ የድምፅ፣ 300 ሜጋ ባይት የኢንተርኔት ዳታና 20 አጭር የጽሑፍ መልእክት በአንድነት - ይህም ከቀድሞው አንፃር የ45 በመቶ ቅናሽ ያለው መኾኑን ገልጿል። (ኢዛ)

ከአገር ውስጥ ይልቅ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የገደለው ኮሮና

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ካሉዋቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ አንዷ እንደምትኾን ይታመናል። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እስከ ሦስት ሚሊዮን ይደርሳሉ።

በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ከሌሎች አገሮች በተለየ በዝተው የሚታዩባቸው አካባቢዎች ናቸው።

በተለያዩ የኑሮና የሥራ ዘርፍ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን የብዛታቸውን ያህል የሚያጋጥሟቸው ስንክ ሳሮች የበዙ ናቸው። ነገሩን ከወትሮው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ካስተሳሰርነውም፤ በየአገሩ ቫይረሱ ከበላቸው የሰው ልጆች መካከል የኛዎቹ ኢትዮጵያውያንም ስማቸው መጠራቱ አልቀረም። በተደራጀ መረጃ ይፋ ባይደረግም በአውሮፓ በተለያዩ አገራት ኢትዮጵያውያን በዚሁ ቫይረስ ሞተዋል። በቫይረሱ የተያዙና ያገገሙም አሉ። በሌሎች አገሮችም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያን የቫይረሱ ሰለባ መኾናቸው ይነገራል።

በዚህ ሳምንት አሳዛኝ ከኾኑ ዜናዎች መካከል ከወደ አሜሪካ የሰማነው ይህንኑ ሥጋት ያጠነክርልናል። በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ቫይረሱ የበዛ ሕዝብ እየገደለባት በምትገኘው አሜሪካ ኢትዮጵያውያን በእጅጉ መጐዳታቸው እየተሰማ ነው። የኢትዮጵያውያን ሞት ከአገር ውስጥ ይበልጥ በውጭ የበረታ መኾኑን አሳይቷል። ከዚህም ከዚያ በተለቃቀመ መረጃ በአሜሪካ ብቻ ከ100 ያላነሱ ኢትዮጵያውያን ስለመሞታቸው በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ አረጋግጠዋል። ዜናው የበለጠ አስደንጋጭ መኾኑን የሚያመለክተን ይህ ቁጥር በኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎች የተገኘ ብቻ መኾኑ ነው።

ነገር ግን በተለያዩ ማኅበራት በኩል ከሚያገኙት መረጃ እንዲሁም በየስቴቶቹ ካሉ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎችና ከመሳሰሉት ካገኙት መረጃ ከ100 ያላነሱ ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን ነው።

በአሜሪካ በዚህ ቫይረስ የተጠቁ የኢትዮጵያውያንን ቁጥር በትክክል ለማግኘት ያልተቻለውና ነገሩ ከፖለቲካ አንፃር በጥያቄ የተያዘ በመኾኑ ምን ያህሉ ኢትዮጵያውያን ሰለባ ኾነዋል ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመሥጠት አስቸግሯል። በአብዛኛው እየሞተ ያለው አፍሪካ አሜሪካውያን በሚል ካታጐሪ የተመደቡ በመኾናቸው፤ ለመለየት አስቸግሯል። እዚህ ውስጥ ግን ኢትዮጵያውያን እንዳሉበት መረዳታቸውን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገልጸዋል።

የአሜሪካ መንግሥት መረጃውን ይፋ ቢያደርግ ደግሞ ቁጥሩ ከዚህም ይልቃል። ይህንን መረጃ የሠጡት አምባሳደር ፍጹም እንደገለጹት፤ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ሞቱ የሚለውን ለማወቅ የግድ የአሜሪካ መንግሥት መረጃውን ይፋ ማድረግ አለበት። አፍሪካ አሜሪካውያን በብዛት እየሞቱ ነው የሚለው መረጃ አሜሪካን ስለሞቱት ሰዎች ዝርዝር ጉዳይ ማውጣት ዳገት ኾኖባታል።

በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብዛት ከሚኖሩባቸው አገሮች መካከል አሜሪካ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሲሆን፤ በአሜሪካ ብቻ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ የሚገመት በመኾኑ፤ ከዚህም በላይ መርዶ ሊሰማ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

አሁን ባለው አኀዛዊ መረጃዎች የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገደለው በእጅጉ በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ምናልባትም በመቶ እጥፍ የሚበልጥ መኾኑ ነው። ይህም ቢሆን ግን ኢትዮጵያውያን ሊረዱ የሚችሉበት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አምባሳደር ፍጹም ገልጸዋል። ወደ ኢትዮጵያ የሚላክ ድጋፍም እየተሰበሰበ ነው። ሌላው አሳዛኙ ነገር ደግሞ በአሜሪካ በዚህ ቫይረስ ሕይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በመንግሥት የሚከናወን መኾኑ ነው። አስክሬን ተቀብሎ ወደ አገር በመላክ የቀብር ሥርዓት ሊፈጸም የማይችል መኾኑም ሌላው ኀዘንን የሚጨምር ጉዳይ ነው። ከኢትዮጵያም ከየትኛውም አገር በኮሮና ቫይረስ የሞተ ሰው አስክሬን እንዳይገባ በመከልከሏም ከዚሁ ጋር ይያያዛል። (ኢዛ)

የባንኮች የገንዘብ እንቅስቃሴ መዳከም

ዓለምን እያንገራገጨ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የኢትዮጵያን የባንክ ዘርፍ እየተፈታተነ ሲሆን፤ በባንክ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውር በእጅጉ እየቀነሰ መኾኑ እየተገለጸ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ የግል ባንኮች መካከል አንዱ የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ዕለታዊ የገንዘብ ዝውውር ከግማሽ በላይ መቀነሱን ገልጿል።

ባንኩ ወረርሽኙን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ርብርብ ላይ የበኩሉን እያበረከተ መኾኑን ለመግለጽ ጠርቶት በነበረ መግለጫው ላይ፤ በቀን እስከ 160 ሺሕ የሚደርስ የገንዘብ ወጪና ገቢ የሚደረግ የነበረው እንቅስቃሴ አሁን ከ100 ሺሕ ወርዷል።

ይህም በቀን እስከ 3.7 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ ያንቀሳቅሱ የነበሩ ቅርንጫፎች፤ አሁን በኢትዮጵያ ወረርሽኙ ሪፖርት ከተደረገበት ጊዜ ወዲህ በቀን እየተንቀሳቀሰ ያለው የገንዘብ መጠን እስከ 1.2 ቢሊዮን ብር (አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር) መውረዱን የሚያመላክት ነው። እንዲህ ያለው ቅናሽ በሁሉም ባንኮች ላይ እየተስተዋለ የመጣ ስለመኾኑም እየተነገረ ነው። በአንፃሩ ባንኮች ወቅታዊውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ተከትለው የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን በመቀነስ ላይ ናቸው። በተለይ ብዙዎቹ ባንኮች ለተበዳሪዎቻቸው የብድር ወለድ ቅናሽ እያደረጉ ሲሆን፤ የተለያዩ አገልግሎቶቻቸው ላይ ቅናሽ አድርገዋል።

በኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክም በሠጠው መግለጫ፤ ለተበዳሪዎቹ ከ0.5 በመቶ እስከ አምስት በመቶ የብድር ወለድ ምጣኔ እንደቀነሰ አስታውቋል። እንደ ብዙዎቹ የባንክ ባለሙያዎች ገለጻ ከበጀት ዓመቱ አጋማሽ ጀምሮ የባንኮቹ እንቅስቃሴ በእጅጉ እየቀነሰ መኾኑን ነው። (ኢዛ)

ኦቢኤንና ከኢትዮጵያ የተሻገረው ቻናል

ከሰሞኑ ከተነገሩ ለየት ያሉ ዜናዎች መካከል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባለቤትነት የሚተዳደረው የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦ.ቢ.ኤን) በምሥራቅ አፍሪካ ተደራሽ የሚኾን ሁለተኛ ቻናል የሙከራ ሥርጭት ስለመጀመሩ መገለጹ ነው። OBN Horn Of Africa በሚል ስያሜ የተሠጠው ይህ ቻናል፤ ስያሜው የተሠጠው በክልሉ መንግሥት ነው።

በዚሁ ጉዳይ ላይ በፌስቡክ ገጻቸው ማብራሪያ የሠጡት የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አዲሱ አረጋ፤ የቻናሉ ዋነኛ ዓላማ የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦችን ማቀራረብ እና ወንድማማችነት ማጠናከር ነው።

የምሥራቅ አፍሪካን ቀጠናዊ ትስስር እውን ለማድረግ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እውን ከማድረግ አኳያ፤ የኦሮሞ ሕዝብ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ለማስቻል ታስቦ የሚተገበር ነው።

ቻናሉ በአፋን ኦሮሞ፣ እንግሊዝኛ፣ ዐረብኛ፣ በሶማሊኛ፣ በትግርኛ፣ በሱዋሂራለ፣ በአፋርኛ፣ በአማርኛ፣ በሲዳሚኛ እና በሌሎች ቋንቋዎች ዜና፣ ፕሮግራሞች እና የመዝናኛ ዝግጅቶች እንደሚያሠራጭም ተጠቅሷል። (ኢዛ)

የቤት መኪኖች እንቅስቃሴ በፈረቃ

በዚህ ሳምንት በቅርቡ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ለወጡት መመሪያዎች አንዱ ተሽከርካሪዎችን የሚመለከት ነው። በኢትዮጵያ የግል ወይም የቤት መኪና አሽከርካሪዎች የሰሌዳ የመጨረሻ ቁጥራቸው ሙሉ እና ጎደሎ በሚል በፈረቃ እንዲያሽከረክሩ የሚያስገድደው ይህ መመሪያ፤ ከሰኞ ሚያዚያ 12 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ ይኾናል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን ደንብ ተከትሎ የትራንስፖርት ዘርፍ አፈፃፀም መመሪያው ይፋ ኾኗል።

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል፤ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ተብሎ የወጣ መኾኑ ተነግሯል።

ይህ መመሪያ አጠቃላይ አምስት ክፍሎች ያሉት እና በ23 አንቀጽ ያለው ነው። በክፍል አንድ አጠቃላይ ድንጋጌዎች፣ በክፍል ሁለት የትራንስፖርት፣ የመናኸሪያ፣ የደረቅ ወደብ እና ሎጅስቲክ አጠቃቀምን የተመለከተ ሲሆን፤ ክፍል ሦስት ደግሞ የሠራተኞች መግቢያና መውጫ ሰዓትን የሚመለከት ነው።

በዚህ መመሪያ ዙሪያ የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን እንዳስታወቀው በመመሪያው የግል ወይም የቤት ተሽከርካሪዎች በፈረቃ እንዲያሽከረክሩ ስለመወሰኑ ገልጿል።

በዚሁ መሠረት የግል ወይም የቤት መኪና አጠቃቀምን በተመለከተ፤ መጠቀም የሚቻለው የሰሌዳቸው የመጨረሻ ቁጥር ሙሉ ወይም ጎዶሎ ቁጥር በሚል በፈረቃ እንዲያሽከረክሩ ተወስኗል።

የሰሌዳ ቁጥራቸው መጨረሻው ዜሮ የኾኑ ተሽከርካሪዎች እንደ ሙሉ ቁጥር ተደርጎ የሚታይ ሙሉ ቁጥር ያላቸው በአንድ ቀን ልዩነት ሲንቀሳቀሱ፤ ጐዶሎ ቁጥር ያላቸውም ሙሉ ቁጥር በማይንቀሳቀሱበት ቀን የሚንቀሳቀሱ ይኾናሉ።

ኾኖም ከሥራቸው ፀባይ አንፃር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ በደንቡ ወይም በመመሪያው የሚሳተፉ ሰዎች ካባለሥልጣኑ በሚሠጣቸው ልዩ የይለፍ ፈቃድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ይደረጋል።

መመሪያው በመላ አገሪቱ ተፈፃሚ የሚኾን ሲሆን፤ የአገር አቋራጭ፣ የከተማ ውስጥ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች በአጠቃላይ ከመደበኛው ወንበር ልካቸው 50 በመቶ ብቻ መኾኑን መመሪያው አመልክቷል።

ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ወይም በተለምዶ ባጃጅ የሚባሉ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ደግሞ፤ መጫን የሚችሉት ከአሽከርካሪው በተጨማሪ አንድ ሰው ብቻ ነው። የመንግሥትም ኾነ የግል ተሽከርካሪዎች በሕግ ከተፈቀደላቸው የመጫን አቅም 50 በመቶ ብቻ እንደኾነም መመሪያው ያመለክታል።

ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና ደንቡ አፈፃፀም ለአገርና ለሕዝብ ደኅንነት አገልግሎት የሚሠጡትን የአገር መከላከያ፣ የፖሊስ፣ አምቡላንስ፣ የእሳት አደጋ እና የመንግሥት መኪኖች የዚህ መመሪያ ድንጋጌ ተፈፃሚ እንደማይኾንባቸው ታውቋል።

ለትራንስፖርት አገልግሎት የተፈቀደ ሰዓትና የታሪፍ ጭማሪን በተመለከተ ማንኛውም የአገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎት መሥጠት የሚችለው ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ባለው ጊዜ ብቻ መኾኑንም ያመላክታል። በዚህ መመሪያ መሠረት አገልግሎቱን ሲሠጡ የታሪፍ ጭማሪ በተመለከተ ከመደበኛ ዋጋው 50 ከመቶ ጭማሪ እንደሚኖረው እና ዝርዝሩ በባለሥልጣኑ እንደሚወሰንም መመሪያው አመላክቷል።

የመናኸሪያ አጠቃቀምን በተመለከተም በዚህ መመሪያ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ መናኸሪያዎች ማስተናገድ የሚችሉት የዕለት ስምሪት ከመደበኛው ጊዜ የስምሪት መጠን 50 በመቶ ብቻ ይኾናል ይላል። ይህ መመሪያ ግን መመሪያው መውጣቱ ከተነገረበት ዓርብ ሚያዝያ 9 ቀን ጀምሮ በተለያዩ ወገኖች እየተተቸ ነው። በተለይ የግል መኪና እንቅስቀሴን ለምን እንዲህ መገደብ አስፈለገ በሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው። የግል ተሽከርካሪዎች ካልተንቀሳቀሱ ባለቤቶቹ በሕዝብ ትራንስፖርት ሊንቀሳቀሱ ነውና ችግሩን ያብሳል እየተባለ ነው። (ኢዛ)

የኮሮና ቫይረስ የበረታባት ጅቡቲና ለኢትዮጵያ ያደረገችው የወደብ ቅናሽ

በአፍሪካ በሕዝብ ብዛታቸው አነስተኛ ከኾኑ አገሮች መካከል አንዷ ከኾነችው ጅቡቲ፤ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ እየተሰማ ያለው ዜና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንፃር ሲታይ አስደንጋጭ ሊባል የሚችል ነው። እስከ ቅዳሜ ሚያዚያ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው በጅቡቲ በቫይረሱ የተጠቁት ሰዎች ቁጥር 732 ደርሷል። አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ነዋሪ ያላት ጅቡቲ በተለይ ከረቡዕ እስከ ዓርብ ባሉት ሦስት ተከታታይ ቀናት 72፣ 156 እና 141 አዳዲስ በቫይረሱ የተጠቁ አዳዲስ ሰዎች ተገኝተዋል።

እንዲህ ባለው ሁኔታ ላይ ያላችው ጅቡቲ፤ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ለኢትዮጵያ እንደ መልካም የታየ ዜና አሰምታለች። ይህም ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ለሚላኩ ዕቃዎች ለወደብ ከምትከፍለው ላይ 82.5 በመቶ ቅናሽ ማድረጓን መግለጿ ነው። ይህንን የጅቡቲን ውሳኔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በፌስቡክ ገጻቸው እንዳመለከቱት፤ “የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ድጋፍ የሚያስፈልጋትን ጎረቤት አገራቸው ኢትዮጵያን በማሰባቸው እጅግ አመሰግናቸዋለሁ!” በሚል የጅቡቲን ውሳኔ አወድሰዋል።

እርምጃው በጋራ አመራር አማካኝነት የኮሮና ቫይረስን ተፅዕኖ የመቋቋም ጥሩ ምሳሌ ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ